
በሕጋዊ መንገድ ተደራጅተው ያለ አግባብ የሚንቀሳቀሱ ደላላዎች ችግር እየፈጠሩ መኾናቸውን አስመጪና ላኪ ነጋዴዎች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 24/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ጉምሩክ ኮሚሽን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በጉሙሩክ አዋጅ፣ በመመሪያው እና የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱን አገልግሎት አሰጣጥ በተመለከተ በባሕር ዳር ከተማ ስልጠና ሰጥቷል። መድረኩ የተዘጋጀው ለአምራቾች፣ ለአስመጪና ላኪዎች፣ ለአስተላላፊዎችና ተጓዳኝ መሥሪያ ቤቶች ነው፡፡
ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ በባሕር ዳር፣ በወረታ፣ በጎንደርና በመተማ መቅረጫና መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች የገቢና ወጪ ንግድ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑ በመድረኩ ተነስቷል፡፡
በዚህም በኮንትሮባንድ የሚገቡና የሚወጡ ልዩ ልዩ ዕቃዎችን በመቆጣጠር፣ ማኅበረሰቡንና ሕጋዊ ነጋዴዎችን በመጠበቅ አመርቂ ውጤት እንደተገኘም ተመላክቷል፡፡

ይሁን እንጂ የውጪ ምንዛሬ ለማስፈቀድና የባንክ ሰነድ ለማሠራት አዲስ አበባ ለመሄድ መገደዳቸው ችግር እንደኾነባቸው ጠቅሰዋል፡፡
በመተማ ደረቅ ወደብ የምድር ሚዛን ባለመኖሩ ለግለሰብ ሚዛን ከፍተኛ ወጪ መጠየቃቸው፣ በቂ የተሸከርካሪ ማቆሚያ አለመኖርና ደላላዎች ያልተገባ ክፍያ እየጠየቁ መኾኑ በአስመጪና ላኪዎች የተነሱ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ የተጠቀሱት ችግሮች መኖራቸውን አረጋግጧል፡፡ ችግሮቹ በጉምሩክ ጽሕፈት ቤት፣ በመስተዳድርና በባለድርሻ አካላት እንደሚፈጠሩም የጽሕፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አለነህ መሐሪ አስታውቀዋል፡፡
በመተማ ጉምሩክ ጣቢያና ወረታ ደረቅ ወደቦች በሕጋዊ መንገድ ተደራጅተው ተመጣጣኝ ያልኾነ እና ደረሰኝ አልባ ክፍያ የሚጠይቁ ደላላዎችን ለማስቆም ከየአካባቢው መስተዳድር አካላት ጋር ውይይት ቢደረግም አልተስተካከለም ብለዋል፡፡ በዚህም አስመጪዎች ተደጋጋሚ ቅሬታ እያቀረቡ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ሀገራዊ የውጪ ምንዛሬ እጥረት እንዳለ ቢታወቅም የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ተገልጋዮች ምንዛሬ ለማግኘት ከሌሎች በተለዬ መልኩ ወረፋ ለመጠበቅ ተገድደዋል፤ ችግሩ የተደራሽነት ችግር መኾኑን በማንሳት ባሕር ዳር ላይ የውጪ ምንዛሬ ፈቃድ የሚሰጥበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እንቅስቃሴ እንደተጀመረ ሥራ አስኪያጅ አመላክተዋል፡፡

ለመተማ ጉምሩክ ጣቢያ 10 ሺህ ካሬ ሜትር የማስፋፊያ ቦታ ቢጠየቅም እስካሁን ምላሽ አላገኘም፤ ለዚህም የጉምሩክ ኮሚሽንን እና የአካባቢውን መስተዳድር ዳተኝነት እንደ ምክንያት ጠቅሰዋል፡፡
ዘመናዊ የምድር ሚዛን አለመኖርም ጊዜ እንዲባክን፣ ግብርም በአግባቡ እንዳይሰበሰብ ምክንያት ኾኗል ነው ያሉት አቶ አለነህ መሐሪ፡፡
ተሽከርካሪዎች ተፈትሸው የሚያልፉበት ስካኒንግ ማሽንም ለመተማ ጉምሩክ ጣቢያ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ጥያቄዎቹ ምላሽ እንዲያገኙ የሚደረገው ጥረት እንደሚቀጥልም አቶ አለነህ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ