
“የማኅበረሰቡን የወተት ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ለመመለስ ዘርፈ ብዙ ጥረት ይጠይቃል” በኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አማካሪ ዮሐንስ ግርማ (ዶክተር)
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 24/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በወተት ምርት የተሰማሩት አቶ ታያቸው አስማረ በዳንግላ ወረዳ ባቻ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ከግብርና ባለሙያዎች ባገኙት የሙያ ድጋፍ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በወተት ማምረት ሥራ ላይ ተሠማርተዋል፡፡ በ1 ሽህ 2 መቶ ብር በገዟት አንድ የውጭ ዝርያ ያላት ጥጃ የጀመሩት የወተት ልማት ዛሬ ጊደሮችን ጨምሮ የ31 ላሞች ባለቤት አድርጓቸዋል፡፡
እንደ አቶ ታያቸው ገለጻ ለሥራው ትኩረት በመስጠታቸው ኑሯቸው ከመሻሻሉ በተጨማሪ በዳንግላ ከተማ ሁለት ቤት ገንብተዋል፤ ልጆቻቸውን አስተምረው ለቁም ነገር አብቅተዋል፤ በዳንግላ ከተማ ለተቋቋመው ሕይወት የወተት ልማት ግብይት ሕብረት ሥራ ማኅበር በቀን ከ98 እስከ 114 ሊትር ወተት ያቀርባሉ፤ በአንድ ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ላይ ስድስት የተለያዬ ዝርያ ያላቸው የእንስሳት መኖ በማልማት ለመኖ ፍጆታ ያውላሉ፡፡ ላሞቹ እንደሚቀርብላቸው የመኖ መጠን እና ዓይነት የሚሠጡት የወተት ምርት ስለሚለያይ ራሳቸው የተመረጡ የመኖ ዝርያዎችን በማምረት እንደሚመግቧቸው ተናግረዋል፡፡
ሕይወት የወተት ልማት ሕብረት ሥራ ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ስሜነህ ማኅበሩ በ1996 ዓ.ም ኅጋዊ ሰውነት አግኝቶ ሥራ መጀመሩን ነግረውናል፡፡ አቶ ተስፋዬ እንዳሉት ማኅበሩ በወቅቱ 200 አባላት ይኑሩት እንጅ በቀን ይቀርብ የነበረው የወተት መጠን ሰባት ሊትር ብቻ ነው ብለዋል፡፡ ማኅበሩ ወተትን ለገበያ ማቅረብ እንደ ነውር የሚቆጠርበትን አመለካከት በመቅረፍ በአሁኑ ወቅት እስከ 4 ሽህ 2 መቶ ሊትር ወተት እየቀረበ ለአካባቢው ማኅበረሰብ እና ለሀገር ውስጥ ገበያ እየዋለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በወቅቱ በ 3 ሽህ 640 ብር ካፒታል የጀመረው ማኅበሩ አሁን 13 ሚሊዮን ብር ካፒታል እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡ አሁን 420 አባላት ሲኖሩት ለ12 ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል፡፡
የአማራ ክልል እንስሳት ሐብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ኀላፊ ደበበ አድማሱ በክልሉ 167 የወተት አምራች አርሶ አደሮች ማኅበራት ተቋቁመው ወተት ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዘርፉ ለወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር፣ የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚ በማሻሻል እና ጤናን በመጠበቅ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ኤጀንሲው አርሶ አደሮች ጥራት ያለው ወተት ከቤተሰብ ባለፈ ለገበያ እንዲያቀርቡ የሙያ፣ የግብዓት እና መሰል ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ኀላፊው ነግረውናል፡፡
በኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ አማካሪ ዮሐንስ ግርማ (ዶክተር) “የማኅበረሰቡን የወተት ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ለመመለስ ዘርፉ ብዙ ጥረት ይጠይቃል” ብለዋል፡፡ አማካሪው እንዳሉት በዘርፉ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ኀይል እጥረት ለመቅረፍ ይሠራልም ብለዋል፡፡
ዶክተሩ እንዳሉት የማኅበረሰቡ የወተት ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሠሩ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የሀገራችን የወተት ሀብት ልማት እንዲስፋፋ ማኅበረሰቡን በዘርፉ ማደራጀት፣ የግብዓት አቅርቦቱ ማሻሻል እና የኤክስቴንሽን ሥራውን መደገፍ ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ