
በአማራ ክልል በየዓመቱ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን ወተት እየተመረተ መኾኑን የክልሉ እንስሳት ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጄንሲ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 24/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የእንስሳት ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጄንሲ በከተማና በገጠር የሚገኙ ዜጎች በዘርፉ እንዲሠማሩ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየሠራ መኾኑን ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ አሚኮ ያነጋገረው የዳንግላ ወረዳ ነዋሪ ወጣት አዲሱ ሞትባይኖር የተሻሻሉ የወተት ላም ዝርያዎችን በመጠቀም በቀን 55 ሊትር ወተት ለተረካቢ ማኅበራት ያስረክባል፡፡ አንድ ሊትር ወተትን በ19 ብር እንደሚያስረክብም ተናግሯል፡፡ በወር ከወጪ ቀሪ እስከ 20 ሺህ ብር ገቢ እንዳለውም ጠቅሷል፡፡ የዘርፉን አዋጪነት በመረዳት ከዚህ በፊት የነበሩ ያልተሻሻሉ ላሞችን በመሸጥ የተሻሻሉ የወተት ላሞችን ማርባቱንም አስረድቷል፡፡
ሌላዋ የዳንግላ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ገነት ፈጠነ የነበሯቸውን ሁለት ያልተሻሻሉ ዝርያ ላሞችንና ችግኝ በመሸጥ አንድ የተሻሻለ ዝርያ ላም በ40 ሺህ ብር መግዛታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከአንድ የወተት ላም የሚያገኙትን ወተት፣ ቅቤ እና አይብ በመሸጥ በወር እስከ 3 ሺህ ብር እንደሚያገኙም አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በፊት ወተት እና አይብ ወደ ከተማ አውጥቶ መሸጥ እንደነውር ሲታይ የነበረውን አመለካከትም መቀየር መቻላቸውን ነግረውናል፡፡ ከቤተሰብ ፍጆታ የተረፈውን ወደ ገበያ በማቅረብ በሚያገኙት ገቢ ልጆቻቸውን ለማስተማርና ቤታቸውን በአግባቡ ለመምራት አስችሏቸዋል፡፡ ዘርፉ በትጋት ከተሠራበት ጥሩ ውጤት የሚያስገኝ በመኾኑ ሌሎች አርሶ አደሮችም እንዲሠማሩበት መክረዋል፡፡
የዳንግላ ወረዳ የእንስሳት ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጥላሁን መስፍን በወረዳው በወተት ሃብትና በማድለብ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ በወተት ልማት ለተሠማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የገበያ ትስስር መፈጠሩን የገለጹት አቶ ጥላሁን የተቋቋሙ ማኅበራት በቀን እስከ 4 ሺህ ሊትር ወተት ተረክበው ወደ አዲስ አበባና ሌሎች አካባቢዎች በመላክ ለተጠቃሚዎች እያደረሱ ነው፡፡
ኀላፊው እንዳሉት ማኅበራቱ መቋቋማቸው ከዚህ በፊት ያለአግባብ ሲባክን የነበረውን ወተት አስቀርተዋል፤ ብዙ አርሶ አደሮችን በዘርፉ በስፋት እንዲሰማሩ አግዟቸዋል፤ ለወጣቶችም የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፤ የተሻለ ሀብት እንዲገኝም አድርጓል ብለዋል፡፡ እየተሠራ ያለውን ውጤታማ ሥራ ለማገዝ የክልሉ መንግሥትም 10 ሺህ ሊትር የሚያጓጉዝ የወተት መሰብሰቢያ ተሽከርካሪ በወረዳው ለተቋቋሙ ማኅበራት በአነስተኛ ወጪ ድጋፍ ማድረጉን አቶ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡
ወረዳው ከማኅበራትና ከክልሉ እንስሳት ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጄንሲ ጋር በመኾን የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን የወተት ላሞች ለማዳረስ አምስት አዳቃይ ባለሙያዎችን በመቅጠር እየሠራ ነው፤ ወረዳውም ለእንስሳት ሀብት የተሻለ ጸጋ አለው ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል የእንስሳት ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጄንሲ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ፈንቴ ቢሻው የወተት ምርት ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ፍላጎቱን ለማርካት ክልሉ በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ ዝርያን ማሻሻል፣ የመኖ አቅርቦትን መጨመር እና የእንስሳት ጤናን ማሻሻል ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የተሻሻሉ የወተት ላሞች የሚገኙባቸውን አካባቢዎች በመለየት አርሶ አደሮቹ ከግጦሽ መሬትም እየቀነሱ መኖ አዘጋጅተው የተሻለ ተጠቃሚ እንዲኾኑ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራቱንም ተናግረዋል፡፡
ከ3 መቶ በላይ አዳቃይ ባለሙያዎች በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ተቀጥረው እንዲሠሩ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡ በሥራውም በየዓመቱ ከ100 ሺህ በላይ የተሻሻሉ ጥጆች ይወለዳሉ፤ ወደ እርባታም ይቀላቀላሉ ተብሏል፡፡
የአማራ ክልል እንስሳት ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጄንሲ መረጃ እንደሚያመለክተው በአማራ ክልል
• ከ16 ሚሊዮን በላይ የዳልጋ ከብቶች አሉ፡፡
• ከእነዚህ ውስጥ 600 ሺህ የሚኾኑት የተሻሻሉ ዝርያዎች ናቸው፡፡
• የእንስሳት እርባታ የክልሉን የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ 24 በመቶ ይሸፍናል፡፡
• በ2012 የበጀት ዓመት ከዘርፉ 19 ቢሊዮን ብር ገቢ ተገንቷል፡፡
• በአማራ ክልል በየዓመቱ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን ወተት እየተመረተ ነው፡፡
•በዚህ በጀት ዓመትም በዘጠኝ ወራት ብቻ 900 ሺህ ቶን ወተት ተሰብስቧል፡፡
• ከሚሰበሰበው ወተት በየቀኑ ከ60 ሺህ ሊትር በላይ ወተት ወደ አዲስ አባባ ይላካል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ