“የሥራ ዕድል ፈጠራዎች በዘላቂነት ለውጥ እንዲያመጡ በጥናትና ምርምር መታገዝ አለባቸው” የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን

489
“የሥራ ዕድል ፈጠራዎች በዘላቂነት ለውጥ እንዲያመጡ በጥናትና ምርምር መታገዝ አለባቸው” የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ለዜጎች የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች በዘላቂነት ለውጥ እንዲያመጡ ለማስቻል በጥናትና ምርምር ማገዝ እንደሚገባ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽነር ንጉሱ ጥላሁን ተናገሩ።
የሥራ ዕድል ፈጠራ አማካሪ ምክር ቤት በሶስት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ባካሄዳቸው ጥናቶች ዛሬ ውይይት አድርጓል።
በመድረኩም አማራጭ የኃይል ልማትና አቅርቦትን ማስፋት፣ የግብርና ምርትን ማጠናከርና ቆዳና ከቆዳ ጋር የተያያዙ ምርቶችን የእሴት ሰንሰለት በማጠናከር ቀጣይነት ያለው ሥራ የሚፈጥሩ የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦች ቀርበዋል።
ምክረ ሃሳቦቹ አስተያየትና ትችት ከተሰጣቸው በኋላ በዕቅድ ውስጥ ተካተው እንደሚተገበሩ ተገልጿል።
ምክር ቤቱ በሥራ ዕድል ፈጠራ ያሉ የህግ ማዕቀፍና የአሠራር ክፍተቶችን የሚሞሉ አማራጭ የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦችን እንደሚቀርቡ ተመልክቷል።
የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ንጉሱ ጥላሁን የሥራ ዕድል ፈጠራ ቀጣይነት ያለው ለውጥ እንዲያስመዘግብ በጥናትና ምርምር የታገዙ ፖሊሲዎችን መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል።
ይህም በግልና በመንግሥት የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎችን በዕውቀት መምራት ያስችላል ነው ያሉት።
በዘርፉ የሚስተዋሉ የአሰራር ችግሮችን ለመፍታትም ጥናትን መሰረት ያደረጉ ምክረ ሃሳቦች ያስፈልጋሉ ብለዋል።
ኮሚሽኑ በጥናትና ምርምር የታገዙ ምክረ ሃሳቦችን ተግባራዊ በማድረግ የሥራ ዕድል የሚፈጠርላቸውን ዜጎች ውጣ ውረድ ለመቀነስ ይሰራል ነው ያሉት።
በዚህም በየዓመቱ የሥራ ገበያውን ለሚቀላቀሉ የ2 ሚሊዮን ዜጎችን ተስፋ ማለምለም ይቻላል ብለዋል።
የአማካሪ ምክር ቤቱ ሊቀመንበር ዶክተር ቴዎድሮስ መኮንን በበኩላቸው ኮሚሽኑ በምክር ቤቱ የተከናወኑ የተካሄዱ ጥናቶችን በመጠቀም ዘርፉን በዕውቀት መምራት እንዳለበት መክረዋል።
ጥናታዊ ጽሁፎችና ምክር ሃሳቦች በፖሊሲ፣ በስትራቴጂና መመሪያ በማካተት ተግባራዊ እንደሚደረጉ የገለጹት ደግሞ የፖሊሲና ስትራቴጂ ዳይሬክተሩ አቶ በዛወርቅ ከተማ ናቸው።
ኮሚሽኑ ይህን እውን ለማድረግ ከባለድርሻ መሥሪያ ቤቶች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በየዓመቱ ለ3 ሚሊየን ዜጎች ሥራ ለመፍጠር የያዘውን እቅድ እውን የሚያደርጉ ምክረ ሃሳቦችን በማቅረብ ረገድ ትልቅ ሚና መጫወቱ ተገልጿል።
ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም በጀማሪ ሥራ ፈጠራ ዓዋጅና የሥራ ላይ ልምምድ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ምክረ ሃሳቦችን አቅርቦ ተግባራዊ መደረጋቸው ለአብነት ቀርቧል።
የሥራ ዕድል ፈጠራ አማካሪ ምክር ቤት ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ 31 አባላትን ያካተተ የባለሙያዎች ቡድን ነው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“በምርጫ ሂደቱ ፓርቲዎች የሰብዓዊ መብቶችን በማክበር በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ መንቀሳቀስ ይገባቸዋል” ኢሰመኮ
Next article“ለሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ትኩረት አለመስጠት ዋጋ እያስከፈለ ነው” በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፓለቲካ ሳይንስ መምህር እና ተመራማሪ ፈቃደ ተረፈ (ዶ.ር)