“በምርጫ ሂደቱ ፓርቲዎች የሰብዓዊ መብቶችን በማክበር በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ መንቀሳቀስ ይገባቸዋል” ኢሰመኮ

138
“በምርጫ ሂደቱ ፓርቲዎች የሰብዓዊ መብቶችን በማክበር በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ መንቀሳቀስ ይገባቸዋል” ኢሰመኮ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በምርጫ ሂደቱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰብአዊ መብቶችን በማክበር በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ።
ኮሚሽኑ በምርጫ ሂደት ሊከበሩ ይገባቸዋል ብሎ ያዘጋጃቸውን ባለ 6 ነጥብ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳ ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያይቷል።
በአጀንዳዎቹ ተጨባጭ የሰብአዊ መብቶች እርምጃዎች ቃል ኪዳን፣ ለሰብአዊ መብቶች በቁርጠኝነት መቆም፣ ከግጭት ቀስቃሽና ከጥላቻ ንግግር መታቀብ የሚሉ ይገኙበታል።
አጀንዳዎቹ በምርጫ ሂደቱ የሚያጋጥሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመቀነስ ፓርቲዎች፣ የፌደራልና የክልል የጸጥታ አካላት ሊያተኩሩባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በዝርዝር አስቀምጠዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ የተዘረዘሩ ነጥቦች የቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ በምርጫው የሚሳተፉ ፓርቲዎች ሁሉ በምርጫ ሂደቱ የሰብአዊ መብቶችን በማክበር በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ መንቀሳቀስ አለባቸው ብለዋል።
በገዥው ፓርቲ የሚፈጸሙ ጥሰቶችን ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደሚያወግዙት ሁሉ በአባላቶቻቸውና ደጋፊዎቻቸው የሚፈጸምን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሊከላከሉና በአጥፊዎች ላይ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል ብለዋል።
ፓርቲዎች በምርጫው ካሸነፉ በተጨባጭ ሊያሻሽሉ የሚችሉባቸው የሰብአዊ መብት አጀንዳዎቻቸውን ለህዝብ ቃል-ኪዳን በመስጠት ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ ንግግሮችና ተግባራት ሊቆጠቡ ይገባልም ነው ያሉት።
የፖለቲካ ምህዳሩ አሁን ላይ በአንፃራዊነት የተሻለ ቢሆንም ከሰብአዊ መብቶች ጥሰት ነጻ አለመሆኑን ጠቅሰው ሁሉም ፓርቲዎች ችግሩን መፍታት አለባቸው ብለዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተዘረዘሩት ነጥቦች አስፈላጊ መሆናቸውን በመጥቀስ ለተግባራዊነታቸው የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ፤ ኮሚሽኑ በምርጫው ሂደት ሊከበሩ ይገባቸዋል ብሎ ያስቀመጣቸውን ነጥቦች ወቅታዊነትና አስፈለጊነት ገልጸዋል።
ፓርቲዎች በሙሉ በምርጫ ሂደቱ ሰብአዊ መብቶችን አክብረው በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ የፈረሙት የቃል ኪዳን ሰነድ መቀመጡን አውስተው ለተግባራዊነቱ እንዲተጉ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በቅድመ ምርጫ፣ ምርጫና ድህረ ምርጫ ጋር በተያዘዘ የሚነሱ የሰብአዊ መብት ሁኔታዎች ላይ ክትትል በማድረግ ተገቢ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዜጎች በምርጫ ሂደቱ መሳተፋቸውን ማረጋገጥና ሌሎች ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጿል።
ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ሙሉ ለሙሉ በተጠናቀቀባቸው አካባቢዎች የድምጽ መስጫ ቀን ሰኔ 14/2013 ዓ.ም መሆኑ ይታወሳል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየሽብርተኛው የህወሓት ቡድን አባላት ላይ የንብረት እግድ የተጣለ መሆኑን የፌዴራል የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።
Next article“የሥራ ዕድል ፈጠራዎች በዘላቂነት ለውጥ እንዲያመጡ በጥናትና ምርምር መታገዝ አለባቸው” የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን