ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል የሚገኙ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን ክልሎቹ አስታወቁ፡፡

211
ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል የሚገኙ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን ክልሎቹ አስታወቁ፡፡
ተፈናቃዮቹ ወደ መኖሪያ ቀያቸው የሚመለሱት አስተማማኝ ሰላም መኖሩ ሲረጋገጥ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽንና የኦሮሚያ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙ ተፈናቃዮችን ጎብኝተዋል፡፡
ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደቡብ ወሎ ዞን በመጠለያ ጣቢያዎች ከ21 ሺህ 680 በላይ ተፈናቃዮች ይገኛሉ፡፡ የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካበቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን፣ የኦሮሚያ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እና የኦሮሚያ ክልል የርእሰ መሥተዳድሩ የሕግ አማካሪ ተፈናቃዮቹ ያሉበትን ወቅታዊ ሁኔታ ተመልክተዋል፡፡
ጉብኝቱ ተፈናቃዮቹን ወደ ቀያቸው መመለስ የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ለመለየት ያለመ ነው ተብሏል፡፡ ዛሬ በኩታበር መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ሁኔታንም ተመልክተዋል፡፡ በመጠለያ ጣቢያው የሚገኙ ወገኖችም የሥራ ኀላፊዎቹ ስለጎበኟቸው አመስግነዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የክልሉን ሰላም አስተማማኝ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡
የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል መንግሥታት በቅንጅት የተፈናቃዮችን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እየሠሩ መሆኑን የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ እታገኘሁ አደመ ተናግረዋል፡፡
ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች ያለው ሰላም አስተማማኝ መሆኑ ሲረጋገጥ በሁለቱ ክልሎች ስምምነት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ምክትል ኮሚሽነር አቶ ገረመው ሆሊቃ ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ መኖሪያ ቀያቸው ለመመለስ የሚያስፈልጉ መረጃዎችን እያሰባሰቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች ወደ መኖሪያ ቀያቸው የሚመለሱት አስተማማኝ ሰላም መኖሩ ሲረጋገጥ መሆኑን ነው ያስታወቁት፡፡
በኦሮሚያ ክልል የርእሰ መሥተዳደድሩ የሕግ አማካሪ አቶ ዳንኤል አሰፋ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው በሕዝቦች መካከል ግጭት እንዲፈጠር የሚሠሩ ኀይሎች እንደነበሩ ገልጸው አሁን ላይ ለችግሩ መዋቅራዊ መፍትሔ ለመስጠት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አሊ ይመር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየአማራ ኤፍ ኤም ጎንደር 105.1 ለጎንደርና አካባቢው ሕዝብ ድምጽ በመሆን ሊሠራ እንደሚገባ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
Next articleየሽብርተኛው የህወሓት ቡድን አባላት ላይ የንብረት እግድ የተጣለ መሆኑን የፌዴራል የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።