
የአማራ ኤፍ ኤም ጎንደር 105.1 ለጎንደርና አካባቢው ሕዝብ ድምጽ በመሆን ሊሠራ እንደሚገባ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ኤፍ ኤም ጎንደር 105.1 ሥርጭት መጀመሩን አስመልክቶ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ወጣት በኀይሉ ፀጋዬ የጎንደር ኤፍ ኤም 105.1 ጣቢያ በዝግጅቶቹ ውስጥ የወጣቶችን በተለይ የተማሪዎችን ፍላጎት በመለየት መሥራት ይጠበቅበታል ብሏል፡፡ “ተማሪው የሚፈልገው ምንድነው፣ የወጣቱ ስነልቦና ምንድነው?” የሚለውን ሐሳብ በመለየት አዲሱ ጣቢያ ተማሪዎችን ያገናዘበ ይዘት በዝግጅቱ ሊያካትት እንደሚገባ ነው ወጣቱ የተናገረው፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋዜጠኝነት የሚማሩ ተማሪዎች ወደ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጎንደር ኤፍ ኤም 105.1 ሲመጡ በንድፈ ሐሳብ የተማሩትን በተግባር እንዲያውሉ ማገዝ እንደሚገባውም አመላክቷል፡፡
ጣቢያው ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች አሳታፊ ማድረግ ይጠበቅበታል ብሏል፡፡ የሬዲዮ ጣቢያው የአካባቢዉን ሕዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችን በስፋት እንዲዳስስም ጠይቋል፡፡
የአማራ ኤፍ ኤም ጎንደር 105.1 በከተሞች የሚስተዋሉትን ችግሮች እየነቀሰ ማውጣትና ለመፍትሔው መሥራት እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ በዕውቀቱ ፍሬው ናቸው፡፡
ሌላኛው ተማሪ አዝማች ተስፋዬ ጣቢያው የአካባቢዉን ባሕል አጉልተው የሚያሳዩ ዝግጅቶችን በመቅረፅ የኅብረተሰቡን ቱባ ባሕል ማስተዋወቅ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሕዝብ ጥያቄ የሆኑትን ጉዳዮች ፈልፍሎ በማውጣት መሥራቱ ተወዳጅና የአድማጭ፣ ተመልካችና አንባቢ ተከታዮቹ ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ተማሪ ከፍያለው ነጋሽ ተናግረዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ችግሮች እንዲፈቱ ከሚሠራው ሥራ በተጨማሪ ጉዳዮቹ የት ደረሱ ብሎ በመጠየቅ መፍትሔ እስኪመጣ ድረስ የሚታገል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ አዲሱ ራዲዮ ጣቢያ ሀገር በቀል በሆኑ ይዘቶች ላይ በማተኮር ጠንክሮ መሥራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡
አዘጋጅ፡- ሐሰን መሐመድ
ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ