ሕጋዊ እውቅና ለተሰጣቸው የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት የመራጮች ትምህርት ሲሰጡ የጸጥታ አካላትም ሆኑ ባለድርሻ አካላት ትብብር ማድረግ እንደሚገባቸው ምርጫ ቦርድ አሳሰበ፡፡

148
ሕጋዊ እውቅና ለተሰጣቸው የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት የመራጮች ትምህርት ሲሰጡ የጸጥታ አካላትም ሆኑ ባለድርሻ አካላት ትብብር ማድረግ እንደሚገባቸው ምርጫ ቦርድ አሳሰበ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመራጮች ትምህርት ላይ ከተሠማሩ የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አመራር አበራ ደገፋ (ዶ.ር) ቦርዱ የመራጮች ትምህርት ለሚያስተምሩ 167 የሲቪክ ማኅበራት ፍቃድ የሰጠ መሆኑን በምክክር መድረኩ ገልጸዋል፡፡ ፈቃድ የተሰጣቸው የሲቪክ ማኅበራት በሰጡት የመራጮች ትምህርት የምርጫ ካርድ የወሰዱ ዜጎች ቁጥር እንዲሻሻል ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና ሰጥተዋል፡፡
ሲቪክ ማኅበራቱ በቀጣይ በሚከናወነው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ዜጎች በንቃት እንዲሣተፉና ድምፃቸውን በነፃነት ለፈለጉት ዕጩ እንዲሰጡ ማሰተማር አሰፈላጊ መሆኑንም ዶክተር አበራ ተናግረዋል፡፡
በድምፅ አሰጣጥ ሂደት በመራጮች መሳሳት ምክንያት የሚባክን ድምፅ እንዳይኖር በመራጮች ትምህርት አሰጣጥ ላይ የተሰማሩ የሲቪክ ማኅበራት ትምህርቱን በተገቢው መስጠት እንደሚኖርባቸውና ድኅረ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን ዜጎች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተገቢው ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
ተሳታፊዎቹ በማስተማር ወቅት የአንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታ ሁኔታ ችግር መኖር እንዲሁም ከቦርዱ የተሰጣቸውን የእውቅና ባጅና ደብዳቤ ቢያሳዩም የመንግሥት የጸጥታ አካላት በማስተማር ወቅት “ከበላይ አካል አልተነገረንም” በሚል ክልከላ በሥራቸው ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል እንደፈጠሩባቸው ገልጸዋል።
ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ የሰጡት ዶክተር አበራ ቦርዱ ለሲቪክ ማኅበራቱ ሕጋዊነት የሰጠው የዕውቅና ሰርተፍኬት፣ ባጅ እንዲሁም ደብዳቤ በቂ እንደሆነና ማንኛውም የመንግሥት ተቋማት የመተባበር ግዴታ ስላለባቸው የመራጮች ትምህርት በሚሰጥባቸው ቀሪ ጊዜያት የጸጥታ አካላትም ሆኑ የባለድርሻ አካላት ትብብር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን መግለጻቸውን ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የጣለውን የጉዞና ተያያዥ ማዕቀብ በመቃወም በካልጋሪ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ።
Next articleየአማራ ኤፍ ኤም ጎንደር 105.1 ለጎንደርና አካባቢው ሕዝብ ድምጽ በመሆን ሊሠራ እንደሚገባ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡