
“ከኢትዮጵያ ጥቅም በተጻራሪ የቆሙ ኃይሎች የሚያራምዱትን የተደራጀና የተቀናጀ ጫና ለመቋቋም ከመንግሥትም ሆነ ከዳያስፖራው ብዙ መሥራት ይጠበቃል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውሳኔን ተከትሎ በኢትዮጵያ ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ጫናዎችን መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የኢፌዴሪ ሚሲዮኖችና ልዩ ልዩ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች የተሳተፉበት በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲና በካናዳ የኢፌዴሪ ኤምባሲ ቅንጅት የተዘጋጀ የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ባስተላለፉት መልዕክት፥ ዳያስፖራው እያከናወነ ያለው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ተግባር አበረታች መሆኑን አንስተዋል፡፡
“ከኢትዮጵያ ጥቅም በተጻራሪ የቆሙ ኃይሎች የሚያራምዱትን የተደራጀና የተቀናጀ ጫና ለመቋቋም ከመንግሥትም ኾነ ከዳያስፖራው ብዙ መሥራት ይጠበቃል” ብለዋል፡፡ እነዚህ ኃይሎች ውስጣዊ ተጋላጭነትን መንጠላጠያ በማድረግና በማደግና በመልማት ጉዞ ላይ እንቅፋት በማበጀት ደካማ ሀገር ሆነን እንድንቀር ስትራቴጂ ነድፈውና ተቀናጅተው እየሠሩ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ዋናው ችግራችን ውስጣዊ መሆኑን ተረድተን ከዚህ አንጻር ሁላችንም ያለንን አቅም አሟጠን በመስራት ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት መንቀሳቀስ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
በውይይቱ የተሳተፉት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ በበኩላቸው መንግሥት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውሳኔን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን ችግር ማቃለል እንዲቻል ልዩ ልዩ ስልቶችን ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ከነዚህም መካከል የውጪ ንግድን ለማስፋፋትና ከዳያስፖራው የሚላከውን የውጭ ምንዛሪ መጠን ለማሳደግ የፖሊሲ አማራጮችን ማየት እንደሚገኝበት አብራርተዋል፡፡ ጫናውን መቋቋምና ይህን ከባድ ጊዜ በጋራ ማለፍ እንዲቻል ዳያስፖራው ገንዘቡን በሕጋዊ የመላኪያ መንገዶች ብቻ ተጠቅሞ እንዲልክ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው፥ ዳያስፖራው ለሀገራዊ ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ጥሪዎች እያደረገ ስላለው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡
ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውሳኔ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ጫናዎችን መቋቋም እንዲቻልም ዳያስፖራው ገንዘቡን በሕጋዊ መንገድ በመላክ፣ መጠኑን በመጨመርና የተጠናከረ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራ በማከናወን ሀገራዊ አለኝታነቱን በድጋሚ ሊያረጋግጥ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ የተሳተፉ የኢፌዴሪ አምባሳደሮች አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ፣ አምባሳደር ፍጹም አረጋ፣ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ እንዲሁም አምባሳደር ዘነበ ከበደ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውሳኔ ሊያስከትላቸው ስለሚችላቸው ጫናዎች፣ ጫናዎቹን ለመቋቋም በየተመደቡባቸው ሀገራት እያከናወኗቸው ስላሉት ተግባራት እንዲሁም በሀገር ቤትና በዳያስፖራው መካከል ቅንጅት በመፍጠር መሠራት ስላለባቸው ተግባራት ዝርዝር ሐሳቦችን አቅርበዋል፡፡
የዳያስፖራ አደረጃጀት ተወካዮችም በበኩላቸው፥ ባከናወኗቸው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራዎች ውጤቶች ቢመዘገቡም በቂ አለመሆናቸውን፣ የተናበበና የተቀናጀ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ በተለይም ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ካላቸው ቁጥር አንጻር በአሜሪካ ምክር ቤቶች ተመራጮች ላይ ተጽዕኗቸውን ለማሳደግ መሥራት እንዳለባቸው ተጠቅሷል፡፡
በመንግሥት በኩል መረጃዎችን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ፣ የሕዝብ ግንኙነትና የኮምዩኒኬሽን ሥራዎችን ለማጠናከር ብሎም በዘርፉ አቅም ያላቸው ተቋማትን በመቅጠር የኃይል ሚዛኑን ለማስተካከል ሊሠራ እንደሚገባ መግለጻቸውን ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
