“ትልማችንም ግባችንም ሚዲያችንን ለኅብረተሰብ ለውጥ እንዲተጋ ማድረግ ነው” የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብርሃም አለኸኝ

95
“ትልማችንም ግባችንም ሚዲያችንን ለኅብረተሰብ ለውጥ እንዲተጋ ማድረግ ነው” የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብርሃም አለኸኝ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ኤፍ ኤም ጎንደር 105.1 ሥርጭት የማስጀመሪያ መርኃግብር ዛሬ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር የሕዝብ ግንኙነትና አደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ እና የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አብርሃም አለኸኝ እንዳሉት አሚኮ በየጊዜው ለውጥ እያመጣ ያለ የሚዲያ ተቋም ነው፡፡ ዘመኑ የመረጃ መሆኑን ያነሱት አቶ አብርሃም ከሌላው ዓለም ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ መረጃ መታጠቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
በተለይ እንደ ኢትዮጵያ አርሶ አደር በሚበዛበት ሀገር የሬዲዮ ተደራሽነትን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑንም ነው አቶ አብርሃም የተናገሩት፡፡
የአማራ ኤፍ ኤም ጎንደር 105.1 የሬዲዮ ጣቢያ የቀጥታ ሥርጭት መጀመር በጎንደርና ዙሪያዋ የሚኖር ማኅበረሰብን እና አርሶአደሮችን ተደራሽ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህም በማእከላዊ መንግሥትና በሕዝቡ፣ በክልሉ መንግሥትና በሕዝቡ መካከል ያለውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስተጋብር ያሳልጣል ብለዋል፡፡
አሚኮ አሁን በስድስት ቋንቋዎች ተደራሽ ነው፡፡ በቀጣይም አፋርኛ፣ ሶማሊኛና ግዕዝን ጨምሮ በሌሎች የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገራት ቋንቋዎች ሥርጭት እንደሚጀምር አቶ አብርሃም አስታውቀዋል፡፡ በተለይም አብዛኛው የኢትዮጵያ ታሪክ የተሰነደው በግዕዝ በመሆኑ “ግዕዝን ወደ መግባቢያ ቋንቋነት ለማምጣት የተጀመሩ ሥራዎች አሉ” ብለዋል፡፡
የቦርድ ሰብሳቢው እንዳሉት ከውስጥም ከውጪም ችግር እየገጠመን ያለው ጠላት ስለ አማራ ሕዝብ የተሳሳተ ትርክት ደጋግሞ ስለተናገረ ነው፤ የአማራን ሕዝብ ትክክለኛ ታሪክ፣ ባሕሉን፣ ሃይማኖቱን፣ የረጅም ጊዜ የመቻቻል መስተጋብሩን ከማስተዋወቅ አንጻር መሠረታዊ ክፍተት መኖሩንም ጠቅሰዋል፡፡ እንደ አቶ አብርሃም ማብራሪያ ይሕንን ለኢትዮጵያና ለዓለም ሕዝብ ማስተዋወቅ ይገባል፤ አሚኮም ትርክቱን ለማስተካከል እየሠራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ለልማት፣ ለትምሕርት፣ ለመልካምና ለጎለበተ አመለካከት መፈጠር እንዲሁም በፖለቲካው መስክ ማኅበረሰቡን መለወጥ እንዲችል ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል ብለዋል፡፡
“ትልማችንም ግባችንም ሚዲያችንን ለኅብረተሰብ ለውጥ እንዲተጋ ማድረግ ነው” ያሉት አቶ አብርሃም ተቋሙ ለሀገር ዕድገትና ለክልሉ ልማት የሚጠበቅበትን እንዲወጣም ሥራ አመራር ቦርዱ ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ይበልጥ ወደ ሕዝብ እየቀረበ ለማገልገል አደረጃጀቱን እና አሠራሩን እያሻሻለ ይገኛል” የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ
Next article“ከኢትዮጵያ ጥቅም በተጻራሪ የቆሙ ኃይሎች የሚያራምዱትን የተደራጀና የተቀናጀ ጫና ለመቋቋም ከመንግሥትም ሆነ ከዳያስፖራው ብዙ መሥራት ይጠበቃል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን