
ሁለተኛው የአማራ ቴሌቪዥን ጣቢያ በመጪው ሰኔ የመጀመሪያ ሳምንት የሙከራ ስርጭት እንደሚጀምር የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) በርካታ ማሻሻያዎችን እያደረገ ይገኛል፤ የማሻሻያው አካል የሆነው ሁለተኛ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሥርጭትም በቅርቡ ይጀምራል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ እንዳሉት በሥራ ላይ ያለው የቴሌቪዥን ጣቢያ በርካታ ዝግጅቶችን እያስተላለፈ ስለሆነ በተለይ በቋንቋዎች ሰፊ የሚዲያ አገልግሎት መስጠት አልቻለም፡፡ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከአማርኛ በተጨማሪ በአዊኛ፣ በኽምጠኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን እያቀረበ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ከስድስቱ ቋንቋዎች በተጨማሪ በቀጣይ ሌሎች የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገራት ቋንቋዎች ዝግጅት እንደሚያስተላልፍ አመላክተዋል፡፡ ይህም የአማራ ሕዝብ ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር ያለውን ወዳጅነት ለማጠናከር፣ ባሕሉን፣ ዕሴቱን፣ ወጉን እና የአኗኗር ዘይቤውን በተለያዩ ቋንቋዎች ለማስገንዘብ ሰፊ እድል እንደሚፈጥር ነው ያመላከቱት፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው መግለጫ ሁለተኛው ጣቢያ አየር ላይ ሲውል ቋንቋዎች የተሻለ ሰዓት እንዲያገኙ ዕድል ይሰጣል፡፡ “የአማራ ሕዝብ በሀገር ውስጥ ከተሠራበት የሐሰት ትርክት ይልቅ በውጪ ሀገራት የተሠራበት ይበልጣል” ያሉት አቶ ሙሉቀን አሚኮ የአማራ ሕዝብን ትክክለኛ ማንነት ለዓለም የማሳወቅ ኀላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የአማራ ሕዝብን ትክክለኛ ማንነት በራሳቸው ቋንቋ ለማስረዳትም በሂደት ተጨማሪ ቋንቋዎች እንደሚከፈቱ ነው ያስታወቁት፡፡ ለዚህም ሁለተኛው የቴሌቪዥን ጣቢያ የሙከራ ስርጭት በሰኔ የመጀመሪያዎቹ ቀናት እንደሚጀምር አመላክተዋል፡፡
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ በጋዜጣ እና በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ወቅታዊ፣ ትክክለኛና ተዓማኒ መረጃዎችን ለሕዝብ እያቀረበ ይገኛል፡፡ የማሻሻያው አካል የሆነው የአማራ ኤፍ ኤም ጎንደር 105.1 ቀጥታ ሥርጭት ዛሬ ይጀምራል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
