
በኢትዮጵያ ላይ የውጭ ኃይሎች እያደረጉትን ያለውን ጣልቃ ገብነትና ጫና ለመመከት እንደሚሠሩ በጣልያን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የመንግሥትን አቋም በመደገፍ የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያለውን ጣልቃ ገብነትና ጫና በመቃወም በጣሊያን ሮም ከተማ ሰልፍ አካሂደዋል።
ሰልፈኞቹ አሜሪካ በኢትዮጵያና በኤርትራ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያላትን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት፣ የሱዳንን የድንበር ወረራ እና በህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ሱዳን እና ግብፅ እየሄዱበት ያለውን ሴራ እና የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን ከኢዲቶሪያል ፖሊሲ ያፈነገጠ ዘገባ ተቃውመዋል ሲል በጣልያን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አመላክቷል፡፡ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ከምዕራባውያን ጫና ሊደረግባቸው ሳይሆን ለተፈናቀሉ እና በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች እገዛ የሚፈልጉበት ወቅት መሆኑንም ገልጸዋል።
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ሙሌት በተያዘለት እቅድ መሰረት እንዲካሄድና ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉም አረጋግጠዋል።
አሸባሪው ሕወሓት አሁንም ከአንዳንድ የውጭ የጥፋት ሽሪኮቹ ጋር የሚያስተላልፈውን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በማጋለጥ ፣ ሰብዓዊ እገዛ እንዲደረግ፣ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል እንዲሁም የኢትዮጵያ አንድነት ለማስጠበቅ ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጎን እንደሚቆሙ እና መከፈል ያለበትን መስዋትነት እንደሚከፍሉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቃል ገብተዋል።
ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ለታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአስር ሽህ ዩሮ ቦንድ ግዢ በመፈጸም አጋርነታቸውን እንደገለጹ ኤምባሲው አስታውቋል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
