ወጣቶች ከመንግሥት ጎን በመቆም የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት እና የውስጥ ተላላኪዎችን ሴራ እንዲያከሽፉ ተጠየቁ፡፡

150
ወጣቶች ከመንግሥት ጎን በመቆም የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት እና የውስጥ ተላላኪዎችን ሴራ እንዲያከሽፉ ተጠየቁ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ ስታዲየም እየተካሄደ ባለው የውጭ ጣልቃ ገብነትን በሚቃወመው ሰልፍ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ምክትል ከንቲበዋ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የገጠሟትን እንደ አድዋ፣ ካራማራ እና ሌሎች ተጋድሎዎችን በመመከት ነጻነቷን አስጠብቃ የቆየች ሀገር መሆኗን ገልጸዋል፡፡
በየጊዜው ወደ ስልጣን የወጡ መሪዎችም ለውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ሳይንበረከኩ ሀገራቸውን በነጻነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፋቸውን አንስተዋል፡፡ ይህ ትውልድም በዚህ ወቅት ሀገሪቱ የገጠማትን ፈተና በመመከት ያባቶቹን ታሪክ ሊደግም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ወይዘሮ አዳነች እንዳሉት ኢትዮጵያ ካለችበት ድህነት ለመውጣት ባላት ተፈጥሮ ሃብት ማንንም በማይጎዳ መልኩ ልማቶችን እያከናወነች ትገኛለች፡፡ በዚህም ማንንም ለመጉዳት እንደማትሻ ሁሉ ኢትዮጵያም እንድትጎዳ የማይፈቅድ ሕዝብ ያላት ሀገር መሆኗን ማሳየት ይገባል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የውጭ ኃይሎች ከውስጥ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ሀገሪቱ የጀመረችውን የልማት እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ እየሠሩ እንደሚገኙም ከንቲባዋ አንስተዋል፡፡ ጣልቃ ገቦቹ በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያውያን ሃብት እና ንብረት እየተገነባ የሚገኘውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውኃ ሙሊትን ለማደናቀፍ እየሠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
“ሀገራችን ዛሬም ሆነ ወደ ፊት ዓባይን በፍትሐዊነት ከመጠቀም የሚከለክላት ኃይል አይኖርም” ብለዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ወጣቶች ከመንግሥት ጎን በመቆም የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት እና የውስጥ ተላላኪዎችን ሴራ ማክሸፍ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መንግሥት በትግራይ ክልል የወሰደውን ሕግ የማስከበር ርምጃ ተከትሎ አሜሪካ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የወሰደችው ርምጃ ተቀባይነት የሌለው ብቻ ሳይሆን መልሰው ሊያጤኑት እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆንም ወጣቱ ጥረት ማድረግ እንዳለበት ወይዘሮ አዳነች ጠይቃዋል፡፡ ወጣቶች እርስ በእርስ ከመጠራጠር በመውጣት ኢትዮጵያዊነትን መንፈስ በመላበስ በጋራ ለሀገር ጥቅም መቆም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በዳግማዊ ተሰራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የአዳማ አዋሽ የፍጥነት መንገድ የወጪና የገቢ ንግድን ለማሳለጥ ወሳኝ ድርሻ አለው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
Next articleየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።