
“የአዳማ አዋሽ የፍጥነት መንገድ የወጪና የገቢ ንግድን ለማሳለጥ ወሳኝ ድርሻ አለው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮ ጂቡቲ የልማት ኮሪደር አካል የሆነው የአዳማ አዋሽ የፍጥነት መንገድ የወጪና የገቢ ንግድን ለማሳለጥ ወሳኝ ድርሻ ያለው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አስታወቁ።
“የአዳማ አዋሽ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ከኢትዮ ጂቡቲ ያለውን የትራንስፖርት መጨናነቅ ከማስወገዱም ባለፈ ረዥም ጉዞ የሚጠይቀውን የወጪና ገቢ ንግድ በማሳለጥ ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ቁልፍ ሚና ያለው ነው” ብለዋል።
በተለይ የኢትዮ ጂቡቲ ኮሪደር የሀገሪቷ 70 በመቶ የወጪና የገቢ ንግድ የሚንቀሳቀስበት በመሆኑ የመንገዶችን ደረጃ ማሳደግ ለሁለንተናዊ ለውጥና ዕድገት የማይተካ ሚና ያለው መሆኑን ተመላክቷል።
“ድህነትና ኋላቀርነት ታሪክ የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የመሰረተ ድንጋይ ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን የጀመርናቸውን ፕሮጀክቶች ጨርሰን ሪቫን እንቆርጣለን” ሲሉም ተናግረዋል።
የአዳማ አዋሽ የፍጥነት መንገድ 130 ኪሎሜትር ይሸፍናል። በመጀመሪያ ምዕራፍ ለሚካሄደው 60 ኪሎሜትር ግንባታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ አስጀምረዋል።
የመንገዱ የግንባታ ወጪ ከአፍሪካ ልማት ባንክ በብድር በተገኘ 6 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የተጀመረ ነው። ሁለተኛ ምዕራፍ 70 ኪሎሜትር ጨረታ ወጥቶ በሂደት ላይ መሆኑ ተገልጿል።
የመንገዱ ግንባታ በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ