
“በውስጣዊ ጉዳዮች ወሳኞች እኛ ኢትዮጵያውያን እንጂ ሌላ የውጭ ኃይል አይሆንም፤ ዕድሉም አይሰጠውም” የአዲስ አበባ ወጣቶች እና በጎ ፈቃድ ማስተባባሪያ ቢሮ ኀላፊ አብርሃም ታደሰ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲስ አበባ ስታዲየም “ድምጻችን ለሉዓላዊነታችን እና ለአንድነታችን” በሚል መሪ መልዕክት እየተካደ ባለው እና የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት በሚቃወም ሰልፍ ላይ የአዲስ አበባ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ኀላፊ አብርሃም ታደሰ መልዕክ አስተላልፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በተለያየ ጊዜ በውጭ ኃይሎች የሚቃጣ ጥቃትን በጋራ በመቆምና በመመከት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እና ሉዓላዊነት ለዘመናት ሳይደፈር እንዲቆይ ማድረጋቸውን ኀላፊው ገልጸዋል፡፡
ከአባቶች የተወረሰውን አኩሪ ተጋድሎ መንግሥታት እና ዘመናት ቢቀያየሩም ወጣቱ ትውልድ እያሥቀጠለው መሆኑን ነው አቶ አብርሃም የገለጹት፡፡ ሰልፉ ወጣቱ ለሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም የማይደራደር መኾኑን ማሳያ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ “በውስጣዊ ጉዳዮች ወሳኞች እኛ ኢትዮጵያውያን እንጂ ሌላ የውጭ ኃይል አይሆንም፤ ዕድሉም አይሰጠውም” ብለዋል፡፡
ሰልፉ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኹለተኛ ዙር የውኃ ሙሊት እና ከድህነት ለመውጣት የሚደረገው ጥረት ያንገበገባቸው የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት ለማውገዝ የተካሄደ መሆኑንም አቶ አብርሃም ገልጸዋል፡፡ የህዳሴ ግድቡ ከድህነት ለመውጣት እንጂ ሌሎችን ለመጉዳት አለመኾኑን መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲኾን የውጭና የውስጥ ኃይሎች በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ የወጣቶች ጥያቄ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አሜሪካ እና አጋሮቿ በተሳሳተ፣ በተዛባ እና በተቀነባበረ የሚዲያ ዘመቻ የያዙትን አቋም እንዲፈትሹም ኀላፊው ጠይቀዋል፡፡
በአዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ