
በአምባሳደር ምስጋኑ አረጋ አስተባባሪነት ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ትምህርት ቤት ተመረቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን እነሞርና ኤነር ወረዳ በአምባሳደር ምስጋኑ አረጋ
አስተባባሪነት ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ትምህርት ቤት ዛሬ ተመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ሚኒስትሮች፣ የደቡብ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር ርስቱ ይርዳው፣ የኦሮሚያ ክልል ርእስ
መሥተዳደር ሽመልስ አብዲሳ ታዋቂ ግለሰቦችን ጨምሮ እንግዶች ታድመዋል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ትምህርት ቤቱን የማስገንባት ህልም የሰነቁት ገና የአንደኛ ደረጃ
ተማሪ ሳሉ መሆኑ ተገልጿል። በቀን ለአራት ሰዓት በእግር ተጉዞ መማር ፈተና ሆኖባቸው ለሁለት ዓመታት ትምህርት አቋርጠው
ወደ ከተማ ለመሰደድ ተገደው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ “ከኔ በኋላ ላሉ ልጆች ያለፍኩት ፈተና እንዳይደገም እፈልግ ነበር” ያሉት
አምባሳደር ምስጋኑ፤ የተለያዩ ግለሰቦችን በማስተባበር ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የያዘ ትምህርት ቤት ማስገንባት እንደቻሉ
ተናግረዋል።
የትምህርት ቤቱ አንደኛ ደረጃ እያንዳንዳቸው 40 ተማሪ የሚይዙ 20 የመማሪያ እና አስተዳደርን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን
የሚሰጡ ክፍሎች እንዳሉት ገልጸዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱም 16 የመማሪያ ክፍሎች፣ የአይሲቲ፣ የላቦራቶሪ፣
የአስተዳደርና ቤተመጻሕፍት ያሉት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ትምህርት ቤቱ ከዚህ ቀደም እስከ ስድስተኛ ክፍል ትምህርት ይሰጥ የነበረ ቢሆንም የተሟላ አገልግሎት አይሰጥም በሚል
ደረጃው ወደ አራተኛ ክፍል ዝቅ የማለት ስጋት ተጋርጦበት እንደነበር አስታውሰው፤ በግላቸው ፕሮጀክት ነድፈው ትምህርት ቤቱ
በአዲስ መልኩ እንዲገነባ ማድረጋቸውን አመላክተዋል።
“አንድን ሰው ሙሉ ትምህርት ቤት ገንባ ማለት ከባድ ነው” ያሉት አምባሳደር ምስጋኑ፤ ከአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ ጀምሮ እስከ
ታዋቂ ባለሀብቶች ድረስ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ለዚህ ውጤት አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
“ፕሮጀክቱ የትብብርና መልሶ የመስጠት ነው” ያሉት አምባሳደሩ ኢትዮጵያን በጋራ የመገንባት ተምሳሌት እንደሚሆንም
ተናግረዋል።
በ1971 ዓ.ም የተመሠረተው ሸብራበር ትምህርት ቤት ነባር ገጽታው ሙሉ ለሙሉ ተቀይሯል። ትምህርት ቤቱ አምፊቲያትር
ያለውና መሆኑም ተመላክቷል፡፡ ዘገባው የኢዜአ ነው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m