
<<በወጀብና በአውሎ ነፋስ መካከል መንገድ አለ፣ ወጀብና አውሎ ነፋስ መንገድ ውስጥም ማሸነፍን ተምረናል>> ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ
ባሕር ዳር: ግንቦት 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ የገቢ ማሰባሰቢያና የምስጋና ዝግጅት በባሕር ዳር ተካሂዷል። በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም ፋሲል ከነማ የአማራ ሕዝብ በስብራቶች ውስጥ ሆኖ ማሸነፍ እንደሚችል፣ ኢትዮጵያውያን በችግር ውስጥ ኾነውም ቢሆን ማሸነፍ ባሕላቸው እንደሆነ ያሳየ የአሸናፊነት ምልክት ነው ብለዋል።
“በወጀብና በአውሎ ነፋስ መካከል መንገድ አለ፣ ወጀብና አውሎ ነፋስ መንገድ ውስጥም ማሸነፍን ተምረናል” ነው ያሉት።
ፈተናዎች እጅጉን ቢበረቱም ከኢትዮጵያውያን በላይ እንዳልሆኑ እንማራለን ብለዋል። የፋሲል ከነማ የቡድን ስሪት የኢትዮጵያ ሥሪት ነው። ትንሿ ኢትዮጵያ ነው፣ ኢትዮጵያውያን አንድ ስንሆን ማሸነፍ በእጃችን እንደሆነ ተምረንበታል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ሕዝብና ተቋማት በአንድ ላይ እጃቸውን የዘረጉት አንድ ስንሆን የማንወጣው ዳገት የማንሻገረው ድልድይ እንደሌለ ለማስተማር ነው ብለዋል።
በሀገራችን ላይ ፈተና ለመደቀን የሚሞክሩትን ኃይሎች አንድ በመሆን ማሸነፍ እንደሚገባም ተናግረዋል። አንድ ስንሆን ስንናገር እንድመጣለን፣ ስንለያይ ብንጮህ እንኳን የሚሰማን የለም ፣ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በሀገራችን ውስጥ ከተጓተትን በአፍሪካም በዓለም የምንሳተፍባቸውን እድሎች እናሳልፋለን፣ አንድ ከሆን ግን በዓለም ደረጃ እንወዳደራለን ነው ያሉት።
ፋሲሎች እንድ እንድንሆን ስላደረጋችሁን እናመስግናለን ብለዋቸዋል። ድሉን ተምሳሌት አድርጋችሁ በአፍሪካ መድረክ መልካም ውጤት እንድታሰመዘግቡም ብለዋል። ተቋማትና ድርጅቶችም የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል። በአልተከሉት ዛፍ ፍሬ አይለቅሙም፣ ድላችንን ዘርተን ኮትኩተን ፣ አሳድገን በጋራ ፍሬውን እንድንበላ በቀጣይም ድጋፍ ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።
በምሽቱ ለፋሲል ከነማ ክለብ ድጋፍ ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ ቃል ተገብቷል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m