
የክልሉ ሕዝብ ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ሁሉ ከምሁራን ጋር እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ፡፡
ባሕር ዳር፡ መስከረም 7/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ በክልሉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚመክር ዓለም አቀፍ ጉባኤ ከመጪው አርብ መስከረም 9/2012 ዓ.ም ጀምሮ በባሕር ዳር ያካሂዳል፡፡
ጉባኤው የአማራ ሕዝብ የፍትህ፣ የሰላም እና የነፃነት ተጠቃሚነት ለኢትዮጵያ አንድነት በሚፈጥርባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደሚሆን የጉባዔው ፕሬዝዳንት ዶክተር ገበያው ጥሩነህ አስታውቀዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ በሚያነሳቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይም በምክክሩ ትኩረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ ውይይቱ ከመስከረም 9 ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ሦስት ቀናት በባሕር ዳር ከተማ እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡
በውይይቱ ለአማራ ሕዝብ ተጠቃሚነት የሚተጉ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚገኙ ምሁራን እንዲሳተፉ ጥሪ ተላልፏል፡፡ 1ሺህ 800 ምሁራን እና ከ700 በላይ ተጋባዥ እንግዶች እንደሚገኙም ተጠቁሟል፡፡ ለውይይቱ መነሻ የሚሆኑ አራት ጥናታዊ ጹሁፎች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በውይይቱ የተለዩ ችግሮችን ለመፍታት እስከ ቀበሌ ድረስ ከሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እንደሚደረግም በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብ ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅቶች እና የማኅበረሰብ አንቂዎች (“አክቲቪስቶች”) ከምሁራን መማክርት ጉባኤው ጋር በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባም መልዕክት ተላልፏል፡፡
ዘጋቢ፡- ሀይሉ ማሞ