
“ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ይገባል” በባሕር ዳር ከተማ የማኀበረሰብ ተኮር ውይይት ተሳታፊዎች
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የማኀበረሰብ ተኮር ውይይት በባሕር ዳር ከተማ
እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ውይይቱ በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የሚታዩ የጸጥታ ችግሮችን መፍትሔ መስጠት ለጋራ አንድነት እና
ብሔራዊ መግባባት በሚኖረው ጠቀሜታ ላይ ያተኮረ ነው፡፡
የመጀመሪያው ዙር ወይይትም ከየካቲት/2013 ዓ.ም ጀምሮ በዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮች ሲካሄድ እንደቆየ ተገልጿል፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ታደገ ነጉ እንዳሉት ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን እንደሚገባ
ተናግረዋል፡፡ የሰላም ጉዳይ እና የወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራም ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡
በሚኖሩበት ቀበሌም የሚፈጠሩ ችግሮችን በእድርና እቁብ ማኅበራዊ ተቋማት መፍትሄ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡
በየደረጃው ከሚገኙ ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሠሩም ጠቅሰዋል፡፡
አቶ ጌታ ተረቀኝ እንዳሉት ደግሞ ሰላም እና ደኅንነትን ለመጠበቅ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ በሀገሪቱ የሚታየው
መፈናቀል እና የጸጥታ ችግር መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
በየአካባቢው የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት በየደረጃው ከሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ጋር እንዴት መሥራት
እንደሚቻል ከመድረኩ ግንዛቤ መያዛቸውንም አብራርተዋል፡፡
የአማራ ክልል የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ የግጭት አፈታት እና መከላከል ዳይሬክቶሬት የሰላም እሴት ከፍተኛ
ባለሙያ አቶ ቸርነት በየነ እንዳሉት ሀገራዊ አንድነትን እና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ዓላማ ያደረገ የመጀመሪያው ዙር
የማኀበረሰብ ተኮር ውይይት ከየካቲት/2013 ዓ.ም ጀምሮ በዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮች ተደርጓል፡፡
በውይይቱም ብሄር ተኮር ጥቃት እንዲቆም በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ የዜጎች ተዘዋውሮ የመሥራ መብት እንዲከበር
ተሳታፊዎች መጠየቃቸውን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
ለተፈናቀሉ ወገኞች የግብዓት ዓቅርቦት ችግር፣ መልሶ የማቋቋም ሥራ መዘግየቱንና ወደ ነበሩበት ከተመለሱ በኋላም
ደኅንነታቸውን ማስጠበቅ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ በውይይቱ ሀሳቦች ተነስተዋል፡፡ በክልሉ እንደ መንገድ፣ ውኃ፣ መብራት እና
መሰል የመሠረተ ልማት ተደራሽነት ችግሮችም በተሳታፊዎች ቀርበዋል፡፡
የተነሱ ችግሮችን በየደረጃው የሚገኙ መስሪያ ቤቶች እንዲፈቱ እንደሚደረግም ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በፌዴራል
እና በክልል የሚመለከታቸው ተቋማት በውይይቱ ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ አቶ ቸርነት ገልጸዋል፡፡
ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ክትትል ይደረጋልም ብለዋል፡፡ ሁለተኛውን ዙር ማኅበረሰብ ተኮር ውይይት አጠናክሮ
ለማስቀጠል እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የውይይት መድረኩ የኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስቴር ከአማራ ክልል የሰላም እና የሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ ጋር በመተባበር
የተዘጋጀ ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m