
ሸጋው ሞጣ ጠቅላላ ሆስፒታል ከ9 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገለት።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአሜሪካ የአልማ አስተባባሪዎች ፈንድ አፈላላጊነት ከምህረት ሜዲካል ሰፕላይ ግሩኘ ግምታቸው ከ9 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ የሕክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ ለሸጋው ሞጣ ጠቅላላ ሆስፒታል ድጋፍ ተደርጎለታል። በቅርቡ ከመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ወደ ጠቅላላ ሆስፒታል ያደገው የሕክምና ተቋሙ የቁሳቁስ ችግሮች ነበሩበት፡፡
የሆስፒታሉ ሐኪም ምግባሩ ጤናው (ዶክተር) የተደረገው ድጋፍ የሆስፒታሉን መሠረታዊ ችግሮች የሚያቃልል ነው ብለዋል። አልጋ፣ ዊልቸር፣ ክራንች እና ሌሎች የሕክምና ቁሳቁስ ተበርክተዋል ያሉት ሐኪሙ በቀጣይም ሌሎች ማኅበራት እና የአካባቢው ተወላጆች ከአልማ ጋር በመተባበር ድጋፍ እንዲያደረጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የምህረት ሜዲካል ስፕላይ ግሩኘ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ መሠረት ዋለ ድጋፉን በማሰባሰብ እና በማስተባበር በኩል አልማ የጎላ አበርክቶ ነበረው ብለዋል። ድርጅታቸው ከዚህ ቀደምም ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከ300 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ የምግብ እና የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ እንዳበረከተም አስታውሰዋል፡፡ ምክትል ሥራ አስኪያጇ ከአልማ ጋር በመሆን በቀጣይም ችግር ያለባቸውን የሕክምና ተቋማት ለማገዝ እንሠራለን ብለዋል። በውጭ የሚኖሩ ሌሎች ድርጅቶች እና ኢትዮጵያዊያንም ተመሳሳይ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ነው ያሉት።
የተደረገው ድጋፍ የሆስፒታሉን መሠረታዊ የቁሳቁስ ችግር እንደሚያቃልል የነገሩን በምሥራቅ ጎጃም ዞን የአልማ ቅርንጫፍ ፕሮጀክቶች ትግበራ አስተባባሪ አቶ አሻግሬ መዝገቡ አልማ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ የሚገኙ ድጋፎችን በማስተባበር እጥረት ላለባቸው ተቋማት ተደራሽ ያደርጋል ብለዋል።
ፕሮጀክት በመቅረጽ ሀብት የማሰባሰብ እና የማፈላለግ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ የገለፁት አቶ አሻግሬ ከዚህ በተጨማሪ ከአልማ ደጋፊ ማኅበራት ጋር በመቀራረብ የማስተባበር ሥራዎችን ይሠራል ብለዋል። ከሀገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት ሲኖራቸው ከአልማ ጋር ቢነጋገሩ ድጋፍ ለተፈለገለት ዓላማ እንዲውል በትብብር እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው -ከሞጣ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ