“ዋንጫውን የአንድ ሳምንት የደስታ መግለጫ ሳይኾን የዘመናት የነጻነት ተምሳሌት ማድረግ ያስፈልጋል” ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ

117
“ዋንጫውን የአንድ ሳምንት የደስታ መግለጫ ሳይኾን የዘመናት የነጻነት ተምሳሌት ማድረግ ያስፈልጋል” ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የዘንድሮው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ አሸናፊ ፋሲል ከነማ እግርኳስ ቡድን ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡ በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ፈንታ ማንደፍሮ (ዶ.ር) ለስኬታማው እግርኳስ ቡድን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የፋሲል ከነማ እግርኳስ ቡድን ስያሜውን የወሰደው ከአሸናፊነት ተምሳሌቱ አፄ ፋሲለደስ በመኾኑ የቡድኑ ስኬት ሀገራዊ አንድምታ አለው ብለዋል፡፡ “በዓለም ላይ የዋንጫ አሸናፊዎች አቀባበል ሥነ ስርዓት የተለመደ ቢኾንም ጠላቶች ከ400 ዓመት በፊት ኢትዮጵያን በጥላቻ ቀብተው በሯ ለዓለም ዝግ እንዲኾን ሲሞክሩ አፄ ፋሲለደስ በአሸናፊነት መርተው ኢትዮጵያ ወደፊት እንድትገሰግስና በነጻነቷ እድትቀጥል ያደረጉትን ድል ስናስታውስ፣ የተለየ ትርጉም ይሰጠበናል” ብለዋል፡፡
“ዋንጫውን የአንድ ሳምንት የደስታ መግለጫ ሳይኾን የዘመናት የነጻነት ተምሳሌት ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል ዶክተር ፈንታ፡፡ ድሉ የመላው ኢትዮጵያውያን እንደኾነም ዶክተር ፈንታ ተናግረዋል፡፡
የስፖርት መርሕ ሕብረት፣ አንድነት፣ ነጻነትና ፍቅር ነው፤ የፋሲል ከነማ አሸናፊነትም ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና በአሸናፊነት እንድታልፍ፣ በነጻነትም እንድትቀጥል አብነት እንደሚኾን ገልጸዋል፡፡ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት በመቆም የሀገሪቱን የነጻነት ዋንጫ በዓለም መድረክ ከፍ ለማድረግ በጋራ እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የፋሲል ከነማ የእግር ኳስ ቡድን በባሕርዳር ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል ከተደረገለት በኋላ በባሕር ዳር ከተማ በተመረጡ ጎዳናዎች ላይም በመዘዋወር ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡
የከተማዋ ሕዝብና የቡድኑ ደጋፊዎችም ፍጹም ሰላማዊ በኾነ መልኩ ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡ በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባዔ ክብርት ወይዘሮ ወርቀሰሙ ማሞን ጨምሮ የአማራ ክልል እና የባሕር ዳር ከተማ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የፋሲል ከነማ እግርኳስ ቡድን ደጋፊዎችና የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡
ዛሬ አመሻሽ ላይ የገቢ ማሰባሰብ መርሃ ግብር እንደሚኖርም ታውቋል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ በአዲስ አበባ ሸራተን አዲስ ኢንተርናሽናል ሆቴል የፋሲል ከነማ እግርኳስ ቡድን የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር መካሄዱ ይታወሳል፡፡
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እያስከተለ ያለውን የከፋ ጉዳት በመረዳት ቅድመ መከላከል ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
Next articleሸጋው ሞጣ ጠቅላላ ሆስፒታል ከ9 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገለት።