“የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት እና ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ የውጭ ኀይሎችን በጋራ መመከት የሚቻልበት ጊዜ አሁን ነው” የአማራ ክልል የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ

169
“የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት እና ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ የውጭ ኀይሎችን በጋራ መመከት የሚቻልበት ጊዜ አሁን ነው” የአማራ ክልል የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስቴር ከአማራ ክልል የሰላም እና የሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ ጋር በመተባበር ሲካሄድ የቆየው የማኅበረሰብ ተኮር ምክክር የመጀመሪያ ዙር አፈጻጸም እና የሁለተኛው ማስጀመሪያ መድረክ እየተካሄደ ነው።
የማኀበረሰብ ተኮር ውይይቱ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከማኀበረሰቡ ጋር በመመካከር የጋራ አንድነትን እና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ዓላማ ያደረገ ነው።
የመጀመሪያው ዙር ምክክር ከየካቲት/2013 ዓ.ም ጀምሮ በዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮች ሲካሄድ እንደቆየ ተነስቷል፤ የነበሩ ችግሮችም በዝርዝር ቀርበዋል።
የአማራ ክልል የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኀላፊ ገደቤ ኀይሉ ኢትዮጵያ በዕድገት ጎዳና ላይ ብትሆንም ከውጭና ከውስጥ በሰላምና ደኅንነት ችግሮች እየተፈተነች ትገኛለች ብለዋል። የችግሮች ዋነኛ ምንጭ ደግሞ ባለፉት ዓመታት ሀገሪቱ የተከተለችው የሀገረ መንግሥት ግንባታ መሆኑን ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም የውስጥ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ አንስተዋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ዜጎች በጋራ በሚያግባቧቸው ጉዳዮች ላይ በሰለጠ መንገድ በመመካከር የመፍትሔ አካል መሆን ሲቻል ነው ብለዋል።
የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት እና ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ የውጭ ኀይሎችን በጋራ መመከት የሚቻልበት ጊዜ አሁን እንደሆነም ተናግረዋል።
ኀላፊው በመጀመሪያው ዙር የማኀበረሰብ ተኮር ምክክር ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
በሁለተኛው ዙር የማኅበረሰብ ተኮር ምክክር ላይ በሰላም አብሮ መኖር፣ መልካም አስተዳደር እና መሠረተ ልማት፣ የሕግ የበላይነት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና የቁጠባ ባህል፣ ሰላማዊ ምርጫና በፌዴራሊዝም ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተገልጿል።
በውይይቱ በክልሉ ከሁሉም ወረዳዎች እና ዞኖች የተውጣጡ የኅብረተስብ ክፍሎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሰራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“በሞታችን የሚያተርፉ እና በቁስላችን የሚነግዱ ሕሊና ቢሶች በዝተዋል፤ ሕዝቡ ነቅቶ ኢትዮጵያን ሊያድንና ወደ ቀደመዉ ክብሯ ሊመልስ ይገባል” የባሕር ዳር የሰላም ልዑክ
Next articleየኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እያስከተለ ያለውን የከፋ ጉዳት በመረዳት ቅድመ መከላከል ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ተገለጸ፡፡