ከባሕር ዳር ጢስ አባይ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ነገ ይጀመራል፡፡

479

ከባሕር ዳር ጢስ አባይ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ነገ ይጀመራል፡፡

ባሕር ዳር፡ መስከረም 7/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት የመሠረተ ልማት ግንባታ ማስጀመሪያና የምረቃ መርሀ ግብሮች ይከናወናሉ፡፡

ከባሕር ዳር ጢስ አባይ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ነገ መስከረም 8/2012 ዓ.ም ይከናወናል፡፡ መንገዱ በ767 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚገነባ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ለአብመድ ገልጿል፡፡

በሁለት ዓመት ከአምስት ወራት እንደሚጠናቀቅም ነው በባለስልጣኑ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ የገለጹት፡፡ የግንባታ ዲዛይን ሥራው እንደተጀመረና የመንገዱ ደረጃም አስፓልት ኮንክሪት እንደሆነ ታውቋል፡፡ መንገዱን የሚገነባውም ሜልኮን የተሰኘ ሀገር በቀል ሥራ ተቋራጭ ነው፡፡

በተያያዘ ዜና ባሕር ዳር ላይ የሚገነባው የአባይ ወንዝ ድልድይ ሥራ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር አርብ መስከረም 9/2012 ዓ.ም እንደሚከናወን አቶ ሳምሶን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ከባሕር ዳር- ዘማ ወንዝ- ፈለገ ብርሃን የሚዘልቀው የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ነገ ይመረቃል፡፡

ለሥራው 2 ቢሊዮን ብር አካባቢ ወጪ እንደተደረገበት ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡ ዋና ዋና ሥራዎች መጠናቀቃቸውን፣ ሞጣ ከተማ ላይ 500 ሜትር የሚሆን የመንገዱ ግንባታ ክፍል እንደሚቀርና ይህንን ጨምሮ ሌሎች ማስተካከያዎች እንደሚከናወኑ አቶ ሳምሶን ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አስማማው በቀለ

Previous articleፈረንሳይ ላልይበላን የመጠገን ቃሏን ልትተገብር ነው፡፡
Next articleየክልሉ ሕዝብ ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ሁሉ ከምሁራን ጋር እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ፡፡