
የቅዱስ ላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥናትና ጥገና ፕሮጀክት በተመለከተ በ5ኛ ዙር የቀረቡ ስምምነቶች ፊርማ ተካሄደ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2013 ዓ.ም (አሚኮ) 5ኛው የቅዱስ ላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥገና ፕሮጀክት ስትሪንግ ኮሚቴ ውይይት እና የስምምነት ፊርማ በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ተካሄደ፡፡ በውይይቱ የቅዱስ ላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሥነ-ሕንፃ መፍትሔ፣ የስትሪንግ ኮሚቴ ውሳኔ፣ የፋይናንስ አጠቃቀም እና የ3D ቴክኖሎጂ ዐውደ ርዕይ ማሳያ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡
በስምምነት ፊርማው ላይ የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ኂሩት ካሳው ‹‹ቅርሳችንን የማዳንና የመታደግ ሥራው ላይ በፍጹም መተማመን ስላገዛችሁን፤ በተግባርም እዚህ ደረጃ ላይ አድርሳችሁ ስላሳያችሁን የፈረንሳይ መንግሥትንና ኢምባሲን ከልብ እናመሰግናለን፡፡ አጠቃላይ ስራው ከቅርሱ ጥገናና ልማት በተጨማሪ ለላልይበላ ከተማ ሌላ ዕሴት የሚጨምር ነው፡፡ በቀጣይም ቃላችሁን እንደጠበቃችሁ ሥራውን ተጠናቆ እንደምንገናኝ ተስፋ አደርጋለሁ››ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ በመተማመን በጋራ ስለሠራን አመሰግናለሁ ብለዋል፡፡ አሁን የተደረጉ ስምምነቶች በቅርሱ ዙሪያ ከዩኔስኮ ጋር የሚኖር ግንኙነትንም ቀላል እንደሚያደርገው ነው የተናገሩት፡፡
በቀረበው ጥናት ውጤት እና በስትሪንግ ኮሚቴ ውሳኔ ላይ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ ለአብያተ ክርስቲያናቱ ጥናትና ጥገና ፕሮጀክት ስምምነቱ በኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ኂሩት ካሳው፣ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ፣ በቅዱስ ላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪ በአባ ፅጌ ስላሴ መዝገቡ እና በፌደራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ፍስሀ መፈረሙን ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ