
አራተኛዉ ዙር የኮዋሽ ፕሮጀክት በ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ተግባራዊ እንደሚሆን የዉኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እና ንጽሕና አጠባበቅ ላይ የሚሠራው የኮዋሽ ፕሮጀክት በ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር አራተኛ ዙር ፕሮጀክት ተግባራዊ እንደሚሆን የዉኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ሚኒስቴሩ አራተኛዉን ዙር የኮዋሽ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሀ ግብር እያከናወነ ይገኛል። በፊንላድ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ በሚከናወነዉ የኮዋሽ ፕሮጀክት በስድስት ክልሎች የሚገኙ 37 ዞኖች 99 ወረዳዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተጠቅሷል።
የኢፌዴሪ የዉኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዲኤታ ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ ኮዋሽ ባለፉት 10 ዓመታት በንጹሕ መጠጥ ዉኃ አቅርቦት እና በንጽሕና አጠባበቅ ዘርፍ ለዉጥ ማምጣቱን ተናግረዋል፡፡
በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም በትግራይ ክልሎች ሦስት ዙር ተግባራዊ በተደረጉት ፕሮጀክቶች በገጠራማ አካባቢ የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በንጹሕ መጠጥ ዉኃ አቅርቦት እና በንጽሕና አጠባበቅ ረገድ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
አራተኛው ዙር የፕሮጀክቱ ትግበራ በፊላንድ መንግሥት የሚደገፍ መሆኑን ዶክተር ነጋሽ ጠቁመዋል፡፡ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም አስታውቀዋል። በዚህ ፕሮጀክት ሲዳማ ክልልን ጨምሮ አማራ፣ ትግራይ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች፣ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።
በፊንላንድ መንግሥት ድጋፍ ለሚተገበረው ፕሮጀክት ዉል መወሰዱን የገለጹት የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር ዲኤታ ወይዘሪት ያስሚን ወሃረቢ ናቸው፡፡ ሚኒስቴር ዲኤታዋ ባለፉት 10 ዓመታት በርካታ ገጠራማ አካባቢዎችን የንጹሕ መጠጥ ዉኃ አቅርቦት ለማሳደግ መሠራቱን አንስተዋል፡፡ የአሁኑን ለየት የሚያደርገዉ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ሥራዎች እንዲከናወኑ መደረጋቸዉ ነዉ ብለዋል።
በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር ኦቲ ሆልፒናና በበኩላቸዉ የኢትዮጵያ መንግሥት የንጹሕ መጠጥ ዉኃ አቅርቦት ላይ እያከናወነ ያለዉ ተግባር የሚበረታታ ነዉ ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ኤልሳ ጉኡሽ – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ