
“በአዲስ አበባ ያለውን የአልማ አባላት ቁጥር እና ገቢን በማሳደግ በኩል ሁሉም ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል” አቶ ጃንጥራር አባይ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአልማ የሴክተር ተቋማት የዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈጻጸም ውይይት እያካሄደ ነው።
ጉባኤው የአማራ አቀፍ ልማት ማኅበር (አልማ) የ2013 የሴክተር ተቋማት የዘጠኝ ወር የእቅድ አፈጻጸም እና ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ተግባራት ላይ ትኩረቱን አድርጓል። የአልማ አባላትና የሥራ ኃላፊዎች በመድረኩ ተገኝተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት አሰተባባሪና የአዲስ አበባ የአልማ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጃንጥራር አባይ እንዳሉት አልማ ለአማራ ሕዝብ የልማት ምልክት እና ፈር ቀዳጅ ማኅበር ነው፡፡ አልማ የሕዝቡን የማኅበራዊ ጥያቄዎች ለመመለስ የተጋ የሕዝብ የልማት ድርጅት ነው ብለዋል፡፡ የአማራ መንገዶች ባለስልጣን ሳይቋቋም ከደባርቅ ቧሂት በየዳ ለመጀመሪያ ጊዜ መንገድ በመሥራት ማኅበራዊ ኀላፊነቱን መወጣት የቻለ የሕዝብ የልማት ድርጅት ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡
በ2002 ዓ.ም ላይ የገቢ ማሳባሰቢያ መርኃግብር በማካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ በክልሉ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች እንዲገነቡ በማድረግ የሥራ አለኝታነቱንም አንስተዋል። ይህ እንዲሆን ደግሞ የአባላትና የደጋፊዎቹ ሚናና ማኅበሩ በሕዝባዊ መሰረት ላይ የቆመ በመሆኑ ዛሬም ትልቅ ኀላፊነቱን እየተወጣ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የክልሉ የድህነት ምጣኔ ከፍተኛ በመሆኑ ችግራችን በአልማ ብቻ አይፈታም ያሉት አቶ ጃንጥራር አልማ በሚችለው ልክ የራሱን ድርሻ ባቀደው ልክ እንዲወጣ ድጋፋቹህ ያልተቋረጠ ሊሆን ይገባልም ብለዋል።
በአዲስ አበባ ያለውን የአልማ አባላት ቁጥር እና ገቢን በማሳደግ በኩል ሁሉም ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል አቶ ጃንጥራር። ለዚህም ደግሞ ከቴሌቶንና ከሲምፖዚየም በመውጣት የራስን አቅም በሕዝባዊ ተሳትፎ ማረጋገጥ እንችላለንም ብለዋል።
በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የአማራ ባህል ማእከልን ለመገንባት የተገኘው 42 ሽህ 200 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የአማራን ሁለንተናዊ ባህልና እሴትን በሚያሳይ መልኩ ገንብቶ ለማጠናቀቅና ታሪክ ለማስቀመጥ በሚከናወነው ተግባር በሀገር ውስጥም ሆነ በባህር ማዶ የሚገኙ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተሳትፏቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴክተር ተቋማት አልማ አስተባባሪ አቶ ይቻላል ኃይሌ ለአልማ የበኩላቸውን እየተወጡ ላሉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አልማ በአማራ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር የሚያጋጥሙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋወች ሲያጋጥሙ የበኩሉን የሚወጣ፣ በትምህርት፣ በጤናና በሥራ እድል ፈጠራ ሕዝቡን በማስተባባር ችግሮችን በመፍታት እየሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ያለውን ትልቅ አቅም በማስተባባር እና የአባላትና የደጋፊዎችን ተሳትፎ በማሳደግ የአልማን አቅም ለማሳደግ የሴክተር ተቋማትን አፈጻጸም እና አቅምን የመገንባት ሥራ እየተከወነ መሆኑን አመላክተዋል።
አልማ በከተማዋ የላቀ ሕዝባዊ ተሳትፎና የላቀ ማኅበራዊ መሰረት እንዲኖረው እየተሠራ በመሆኑ በዚህ ዓመት ብቻ ከ1 ሽህ 200 በላይ አዳዲስ አባላትን ማፍራት መቻሉን አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአልማ የሴክተር ተቋማት የ2013 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
አልማ ባለፉት 9 ወራት አዳዲስ የኮርፖሬት አባላት ማፍራት፣ ለአማራ ባህል ማእከል 11 ሚሊየን ብር ማሰባሰብ መቻሉ፣ ለተፈናቃሉ ወገኖች ከ3 ሚሊየን 700 ሽህ በላይ በጥሬና በአይነት ድጋፍ መደረጉና አዳዲስ አባላትን ማፍራት መቻሉ በጥንካሬ ተነስቷል።
የመደበኛ አባላትን ክፍያ በወቅቱ አለመሰብሰብ፣ ወቅታዊ መረጃዎችን ይዞ ተልዕኮን በወቅቱ አለመፈጸም እና በተጠናከረ መልኩ ኮርፖሬትን በእቅድ ልክ አለመሥራት ደግሞ በድክመት ከተነሱት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ