አሜሪካ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የጣለችው የጉዞ እገዳ በአፍሪካ ያላትን ጥቅም ሊያሳጣት እንደሚችል ተገለጸ፡፡

165
አሜሪካ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የጣለችው የጉዞ እገዳ በአፍሪካ ያላትን ጥቅም ሊያሳጣት እንደሚችል ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሜሪካ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ ያሳለፈችው የጉዞ እገዳ ውሳኔ በቀጠናው ያላትን ጥቅም ሊያሳጣት እንደሚችል አሚኮ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ምሁራን ተናግረዋል፡፡ የዓለም ሰላምና ሰብዓዊ መብት መከበርን እንደ ሽፋን በመጠቀም ለራሷ ጥቅም እንደምትሠራ አብራርተዋል፡፡ በማንኛውም መንገድ ከፍላጎቷ በተጻራሪ በሚቆም ወይንም ሊታዘዝላት ፈቃደኛ በማይኾን መንግሥት ላይ ማዕቀብ የመጣልና ተከታታይ ርምጃ የመውሰድ ልምድ እንዳላትም አስታውሰዋል፡፡
ሊበራሊዝምን የምትሰብከው አሜሪካ በሞራላዊና ሕጋዊ ዓለም አቀፍ ትብብር ስም ምላ ብትገዘትም ከራሷ ብሔራዊ ጥቅም ውጪ ግድ እንደማይላት በተግባር እየታየ መሆኑን የወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ጀማል ሰዒድ አብራርተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ያራመደችው አቋም ከዚህ የተለየ እንዳልሆነም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ጥናት መምህሩ ታደሠ አክሎግ (ዶክተር) ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ ውሳኔው ከኢትዮጵያም አልፎ በአፍሪካ ያላትን ጥቅም ሊያሳጣት እንደሚችል ምሁራኑ አብራርተዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኀያላን ሀገራት አሰላለፍና ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ተቀያያሪ ነው፡፡
አቶ ጀማል እንዳሉት የአሜሪካ አካሄድ አደገኛና የባለብዙ ሀገራት ስምምነትን ችግር ውስጥ የሚጥል ነው፤ እንደ ዓለም ባንክ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋምና ዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅቶችን ተዓማኒነትም ይጎዳል። ይህም ተመልሶ የራሷን ብሔራዊ ጥቅም እንደሚጎዳ ተናግረዋል። እንደ መምህራኑ ማብራሪያ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፈችው ውሳኔ በአፍሪካ ያላትን ተቀባይነት ይሸረሽራል፤ በተቃራኒው የተገዳዳሪ ሀገራትን ተዓማኒነትና ተቀባይነት በማሳደግ በአፍሪካ ለሚያደርጉት ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ምቹ መደላድል ይፈጥላቸዋል፡፡
ምንም ይሁን ምን ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስከብር አካሄድ መከተል ይኖርባታል፡፡ ምሁራኑ እንደሚሉት ምቹ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና ከፍተኛ አምራች ኀይል ያላት ኢትዮጵያ ከውጪ በሚደረግ ድጋፍ ላይ የተመሠረተው ኢኮኖሚዋ ለውጥ ማምጣት አልቻለም፡፡ ከሰሞኑ የተላለፈው ውሳኔም የኢትዮጵያን የመልማት እንቅስቃሴ ሊወስን እንደማይችል አመላክተዋል፡፡ ይልቁንም ሀገራዊ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሁኔታን ለማስተካከል እንደ ማንቂያ ደውል ሊኾን ይገባል ነው ያሉት፡፡
ውስጣዊ የፖለቲካ ችግሮች ተፈትተው አንድነትን ማጠንከር ካልተቻለ ችግሩ ሊስተካከል ስለማይችል ውስጣዊ ሰላምን ማረጋገጥ፣ ዴሞክራሲን ማጎልበትና ሀገሪቱ በሁለት እግሯ እንድትቆም ማስቻል ዋንኛው መፍትሔ እንደሆነ መክረዋል። የኢኮኖሚ አቅሟን መጠቃም፣ የውስጥ ችግሮቿን በራሷ አቅም መፍታት፣ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናን እንደ ኢኮኖሚ አማራጭ መጠቀም፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር ትኩረት መስጠት እና የራሷን እድል የመወሰን መብቷን ማስጠበቅም ከኢትዮጵያ ይጠበቃል።
ለውጭ ኀይል ተጋላጭ ሊያደርጉ የሚችሉ የውስጥ ችግሮችን በመፍታትና የፖለቲካ ሁኔታን በማስተካከል ኢንቨስትመንትን ማስፋፋትም ያስፈልጋል፡፡ ምሁራኑ እንዳሉት የሰሞኑን ውሳኔ ተከትሎ የኢትዮጵያ አካሄድ ስልታዊ መኾን አለበት፤ ከአሜሪካ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ መግባት አይገባም ብለዋል፡፡
በተቻለ መጠን የዘመናት ወዳጅነትን ለማስቀጠል መጣር ይገባል ያሉት ዶክተር ታደሰ ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚኖራት ግንኙነት እንዳይቀዛቀዝም የኢትዮጵያ መሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከሀገራት ጋር የምታደርገው ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅሟን ታሳቢ ያደረገ እንጂ ሀገር የመጉዳት ዓላማ የላትም፡፡ ይሁን እንጂ በዲፕሎማሲው መስክ ድክመት እንደሚስተዋልባት ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በኀይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበራት ዲፕሎማሲያዊ ተቀባይነትና ተጽእኖ ፈጣሪነት ከፍተኛ እንደነበርም ምሁራኑ ጠቅሰዋል። ምሁራኑ እንዳሉት ከዚያ ወዲህ የውጪ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ጉዳይ ትኩረት ተነፍጎታል፤ ይህም ኢትዮጵያ የአጎራባች ሀገራትን ሁኔታና ዓለም አቀፍ ክስተቶችን ያማከለ እንቅስቃሴ እንዳትከተል አድርጓታል፡፡ ችግሩን ለመፍታትም የዘመኑን ተለዋዋጭ ባሕሪ በሚገባ የሚገነዘቡ እንዲሁም በሙያው የዳበረ ልምድና ብቃት ያላቸውን ዲፕሎማቶች ማሰማራት እንደሚገባ መክረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ኢትዮጵያን የአፍሪካ ኢኖቬሽን መዳረሻ ለማድረግ እየተሠራ ነው” የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)
Next article“በአዲስ አበባ ያለውን የአልማ አባላት ቁጥር እና ገቢን በማሳደግ በኩል ሁሉም ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል” አቶ ጃንጥራር አባይ