“ኢትዮጵያን የአፍሪካ ኢኖቬሽን መዳረሻ ለማድረግ እየተሠራ ነው” የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)

116
“ኢትዮጵያን የአፍሪካ ኢኖቬሽን መዳረሻ ለማድረግ እየተሠራ ነው” የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2013 ዓ.ም (አሚኮ) “አዲሷን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መዳረሻ ኢትዮጵያን እናስስ” በሚል ከፍተኛ የመንግሥት ኀላፊዎችና የአሜሪካ ባለሃብቶች የተሳተፉበት የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት እያከናወነቻቸው ያሉ ሥራዎች ገለጻ ተደርጓል፡፡
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍፁም አረጋ መንግሥት ምቹ የንግድ ከባቢ ሁኔታን ለመፍጠርና የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ የተለያዩ የሕግ ማሻሻያዎች እያደረገ ነው ብለዋል።
በግሉ ዘርፍ የሚመራ ኢኮኖሚን ለመገንባትም የንግድ ሕግ ማሻሻያ መደረጉንና የኢንቨስትመንት አዋጅ መውጣቱን ጠቁመዋል ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችላትን የዘርፉን ማሻሻያዎች በማድረግ የዲጂታል መሰረት እየጣለች መሆኑን ተናግረዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂና የኤሌክትሮኒክስ ትራንዛክሽን አዋጅ መፅደቁ፣ የዲጂታል መታወቂያ ወደ ትግበራ መግባት፣ የስታርት አፕና የግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ በረቂቅ ሂደት ላይ መሆናቸው፣ የመንግሥት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት፣ ኤሌክትሮኒክስ ግብይት (ኢኮሜርስ) እና የመሳሰሉት ኢትዮጵያ በልዩ ትኩረት እየሠራችባቸው ስለመሆኑ አመላክተዋል።
ኢትዮጵያን “የአፍሪካ ኢኖቬሽን መዳረሻ” የማድረግ እቅድ ያለው ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካሪ ሜሪያም ሰይድ ኢትዮጵያ ከመንግሥት መር ኢኮኖሚ በግሉ ዘርፍ ወደሚመራ ኢኮኖሚ ሽግግር እያደረገች ነው ብለዋል።
የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ተዋናይ እንዲሆን ለማድረግም የንግድ ሥራ ቅልጥፍና ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው ያሉት አማካሪዋ የቴሌኮም ዘርፉን በከፊል ወደ ግል የማዞር ሥራ፣ የዲጂታል ክህሎት ግንባታ፣ የመረጃ መረብ ደኅንነት ጥበቃ፣ የግለሰብ የመረጃ ጥበቃ አዋጅ ለዘርፉ መደላድል ለመፍጠር እየተሠራባቸው መሆኑን አብራርተዋል።
የአሜሪካ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለውን የዘርፉን ማሻሻያ እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ እንደቀረበላቸው መገለጹን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየዘንገና ሐይቅ ዳርቻን በማልማት ለጎብኚዎች ምቹ ማድረግ እንደሚገባ የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
Next articleአሜሪካ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የጣለችው የጉዞ እገዳ በአፍሪካ ያላትን ጥቅም ሊያሳጣት እንደሚችል ተገለጸ፡፡