
የዘንገና ሐይቅ ዳርቻን በማልማት ለጎብኚዎች ምቹ ማድረግ እንደሚገባ የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የዘንገና ሐይቅን የጉብኝት መዳረሻ ማድረግ እና የሚመጡ ጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ የተሻለ የሚያደርጉ የእንግዳ ማረፊያዎች እና ሆቴሎች ሊገነቡ እንደሚገባ የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
የተፈጥሮ ልዩ ገጽ በረከት የኾነው ዘንገና ሐይቅ በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ባንጃ ወረዳ ከሳ ቸውሳ ቀበሌ የሚገኝ ውብ ሥፍራ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ በ430 ኪሎ ሜትር፣ ከባሕር ዳር በ132 ኪሎ ሜትር፣ ከእንጅባራ ከተማ ደግሞ በአምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል – ዘንገና ሐይቅ፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ 930 ሜትር ርዝመት አለው፡፡ የሐይቁ ጥልቀትም እስከ 169 ሜትር ይደርሳል፤ ከ75 በላይ የእፅዋት ዝርያዎች፣ የዱር እንስሳት እና አዕዋፋት በዙሪያው እንደሚገኙም ከባንጃ ወረዳ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
የሐይቁ አካባቢ ትኩረት ተሰጥቶት ቢለማ ለገበታ ለሀገር ከሚሠሩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ማለትም ጎርጎራ፣ ወንጪና ኮይሻ ተርታ ሊሰለፍ የሚችል መሆኑን ለጉብኝት በቦታው የተገኙ ሰዎች ትዝብታቸውን ይገልጻሉ፡፡ እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ፣ አስተማማኝ ሠላም፣ ተስማሚ የአየር ጸባይ እና መሰል ምቹ ሁኔታዎችን የታደለ ነው፡፡ ከብሔረሰብ አስተዳደሩ ዋና ከተማ እንጅባራ በቅርብ ርቀት የሚገኝ በመሆኑ ለመሰረተ ልማት ቅርብ ነው፡፡
አሚኮ በቦታው ተገኝቶ መመልከት እንደቻለው በሐይቁ አካባቢ እስከ ሐይቁ ዳርቻ ማስገባት የሚችል መንገድ ተሠርቷል፤ አምስት አስጎብኚዎች ብቻ ሐይቁን በማስተዋወቅ ሥራ ተሠማርተዋል፤ ሊሠራ ታቅዶ በጅምር 11 ዓመታትን ያህል ያስቆጠረ የእንግዳ ማረፊያም በአቅራቢያው ታዝበናል፡፡
ወጣት አበበ በቀለ የባንጃ ወረዳ ነዋሪ ነው፡፡ ወጣቱ እንደገለጸው ሐይቁ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል ቢሆንም ትኩረት ተስጥቶት እየለማ አይደለም፡፡ የአካባቢው ነዋሪ በዙሪያው ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ የሐይቁን ሕልውና እያስጠበቁት እንደሚገኝም ተናግሯል፡፡ “ሐይቁ ታይቶ የማይጠገብ ነው” ያለው አበበ የሐይቁ ዳር መሰረት ልማቶች ተገቢ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊሻሻሉ እንደሚገባ ገልጿል፡፡
አካባቢውን ማልማት እና ዘርፉን ማዘመን አለመቻሉ ለብዙ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር እየቻለ “የበይ ተመልካች” እንዳደረጋቸው ተናግሯል፡፡ በሐይቁ አካባቢ የመኪና ማቆሚያ፣ ደረጃውን የጠበቀ መንገድ፣ አግልግሎት ሰጪ ተቋማት እና የእንግዳ ማረፊያዎች ሊስፋፉ ይገባል ባይ ነው፡፡
የዘንገና ሐይቅና አካባቢው አስጎብኚ ወጣት ዮናስ መኩሪያው “ዘንገና ሐይቅ የብሔረሰብ አስተዳደሩ እንቁ የቱሪስት መዳረሻ ነው” ሲል ገልጿል፡፡ ሐይቁ ከእንጅባራ ከተማ በቅርብ ርቀት የሚገኝ በመሆኑ በየቀኑ በአማካይ ከ50 እስከ 200 የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች እንደሚጎበኙት ተናግሯል፡፡ በብዙኃን መገናኛ፣ ፊልም እና ሙዚቃ ከሚሠሩ ባለሙያዎች ጋር እና የተለያዩ የህትመት ውጤቶችን በመጠቀም ሐይቁን ለጎብኚዎች ለማስተዋወቅ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውንም ነግሮናል፡፡
በባንጃ ወረዳ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቱሪስት መዳረሻ ልማት ባለሙያ አንዱዓለም ይግዛው እንደገለጹት ዘንገና ሐይቅን በማስተዋወቅ የጉብኝዎች መዳረሻ ለማድረግ እየሠሩ ነው፡፡ ከእንጅባራ ከተማ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት ጎብኚዎች ስለ ሐይቁ እና የቱሪዝም መዳረሻዎችን በተመለከተ በቂ መረጃ እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ዘውዲቱ ወርቁ እንደተናገሩት ብሔረሰብ አስተዳደሩ ውብ ሐይቆች፣ ፏፏቴዎች፣ ሰፊ የደን ሃብት፣ ትልልቅ ዋሻዎች፣ ገዳማት እና በመሰል ታሪካዊ እና ተፈጥሮአዊ መስህብ ሀብቶች የታደለ ነው፡፡ ባሕልና ቱሪዝም መምሪያው ሃብት በማሰባሰብ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስዋብ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
የመዳረሻ ቦታዎችን በማልማቱ ረገድ እንጅባራ ዩኒቨርሲቲም ዘርፈ ብዙ እገዛ እያደረገ መሆኑን ኀላፊዋ ጠቅሰዋል፡፡ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ልዩ መገለጫ የኾነውን የዘንገና ሐይቅ ዳርቻዎችን ለማልማት ከባለሃብቶች ጋር እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከ400 ሺህ ብር በላይ ተመድቦ እስከ ሐይቁ የሚያደርሰው መንገድ እየተሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ኅብረተሰቡ እንግዳ አክባሪ፣ የተሻለ ሠላምና ምቹ የአየር ጸባይ የታደለ አካባቢ በመሆኑ ሐይቁን በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የሚገኙ ዜጎች እንዲጎበኙት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ወለሌ ጌጤ በሐይቁ አካባቢ ለ11 ዓመታት ቆሞ የሚገኘው የህንፃ ግንባታ ለምን መጠናቀቅ አልቻለም? ብለን ጠይቀናቸው ነበር፡፡ ኀላፊው እንደገለጹት በመጀመሪያ ግንባታው ያረፈበት ቦታ ለሐይቁ ሕልውና አደጋ ነበር፤ በመሆኑም ግንባታው እንዲቆም ተደርጓል፤ ኢንቨስትመንት መምሪያው ፈቃዳቸውንም ሰርዟል፡፡ የሐይቁን ሥነ ምህዳር በማይጎዳ መልኩ አካባቢውን ለማልማት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ኀላፊው ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ