
“በኢትዮጵያ ደካማና ተላላኪ መንግሥት ለመፍጠር የሚሹ ሀገራት አይሳካላቸውም” የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ደካማና ተላላኪ መንግሥት ለመፍጠር የሚሹ ሀገራት ጥረታቸው ፍፁም የማይሳካ መሆኑን የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች ገለጹ።
“ኑ ኦሮሚያን እናልብሳት” የአረንጓዴ አሻራ የተለያዩ የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች በተገኙበት ተጀምሯል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተናገሩት ርእሳነ መስተዳድሮቹ ኢትዮጵያ ደካማና ተላላኪ መንግስት ለመፍጠር የሚሹ ሀገራት ጥረታቸው ፍፁም የማይሳካ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን አንድነት ለመከፋፈልና በትንንሽ ክልሎችና ደካማ ሀገር ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ተቀባይነት የሌለውና የተሳሳተ አካሄድ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፤ የውጭ ኀይሎች በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ ሽግግር እንዳይኖርና ደካማ መንግሥት ለመፍጠር እየሰሩ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
በድጋፍ ሰበብ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለመድፈር የሚያደርጉት ጥረት ተቀባይነት የሌለውና ፍፁም የማይሳካ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሁላችንም በአንድነት ፊታችንን ወደ ልማት በማዞር ከውጭ አገራት ጥገኝነት እራሳችንን ለማላቀቅ መሥራት ይኖብናል ብለዋል።
ስንዴ እየሰጡ ለዘመናት በድህነት ውስጥ እንድንኖር የሚሹ ሀገራት መኖራቸውን ጠቅሰው ከዚህ ለመውጣት በትብብር ጠንክረን መስራት ይኖርብናል ብለዋል።
ከውጭ ሀገር ስንዴ አንለምንም፣ አንቀበልም በዚህ ዓመት በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአስተራረስ ስልት በመጠቀም ምርትና ምርታማነት ላይ የሠራናውንና ውጤት ያገኘንበትን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።
የውጭ ጣልቃ ገብነት አንቀበልም፣ በሀገር ውስጥ በርካታ ምርት በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማስፋት እንሠራለን ሲሉም አረጋግጠዋል። ኢዜአ እንደዘገበው
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አገኘው ተሻገር በበኩላቸው ደካማና ተላላኪ መንግሥት ለመፍጠር የሚሹ ኀይሎች ጥረታቸው ፍፁም አይሳካም ብለዋል።
የውጭ ኀይሎች የኢትዮጵያን አንድነት በመሸርሸር ደካማ አገር ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት ሁላችንም በመረዳት በጋራ መመከት አለብን ብለዋል።
የአገር ውስጥ ተላላኪ ባንዳዎችን በአንድነት ሆነን በጋራ ልንታገላቸው ይገባልም ነው ያሉት።
የውጭ ኀይሎች ለዘመናት ኢትዮጵያ በራሷ ሀብት እንዳትጠቀምና ከድህነት እንዳትወጣ ያደርጉት የነበረውን ጥረት አሁንም ቀጥለውበታል ያሉት ደግሞ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳው ናቸው።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ላዴሞ የአሜሪካ መንግስት በተደራደሩ ሰበብ የሞተውን ሥርዓት ከመቃብር ለማንሳት የሚያደረገው ጫና ተቃባይነት የለውም ብለዋል።
በዚህ ሰበብ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው ጫና ተቀባይነት የሌለው ድርጊት በመሆኑ ሁችንም በጋራ ልናወግዘው ይገባል ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ ይሞላል፣ ምርጫውም በጋራ ጥረታችንና በህዝቡ ድጋፍ ስኬታማ ይሆናል ብለዋል ርእሳነ መስተዳድሮቹ።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m