
ፈረንሳይ ላልይበላን የመጠገን ቃሏን ልትተገብር ነው፡፡
ባሕር ዳር፡ መስከረም 7/2012 ዓ.ም (አብመድ) ፈረንሳይ የደብረ ሮሐ ቅዱስ ላል ይበላ አብያተ ክርስቲያናትን ጥገና በቅርብ እንደምትጀምር የሀገሪቱ የባሕል ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ የፈረንሳይ የባሕል ሚኒስቴር ሚኒስትር ፍራንክ ሬስተር የደብረ ሮሐ ቅዱስ ላል ይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ዛሬ ጎብኝተዋል፡፡
የደብረ ሮሐ ቅዱስ ላል ይበላ አብያተ ክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ አባ ፅጌ ስላሴ መዝገቡ ለአብመድ እንደገለጹት ሚኒስትሩ ወደ ስፍራው የመጡት አብያተ ክርስቲያናቱን ለመጎብኘት እና ጥገናው የሚጀመርበትን መንገድ ለማመቻች ነው፡፡
ከሚኒስትሩ ጋር ታዋቂ ባለሙያዎች ወደ ስፍራው እንደመጡ የገለጹት አባ ፅጌ ስላሴ ባለሙያዎች ጥናት አድርገው በቅርቡ ሥራ እንደሚጀመር እና ክትትልም እንደሚያደርጉለት ሚኒስተሩ መግለጻቸውን አስታውቀዋል፡፡ ባለሙያዎች ከአሁን በፊት መጥተው አስፈላጊ መረጃ እንደወሰዱም ነው የተገለጸው፡፡
“ላል ይበላ የኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን የሰው ዘር ሁሉ ቅርስ ነው፤ የሰው ልጅ ይህን በመስራቱ ሁላችንም ልንኮራ ይገባል፤ ከሰማነው ነገር ሁሉ የላቀ ድንቅ ስፍራ ነው›› ብለዋል ሚኒስትሩ ፍራንክ ሬስተር፡፡ ለሥራውም ትኩረት እንደሚሰጡት ቃል መግባታቸው ታውቋል፡፡
ዘጋቢ፡-ታርቆ ክንዴ