
ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ በፋይናንስና በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዘርፍ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸው የግንባታው አፈጻጸም
ቀጣይነት እንዲኖረው እንዳስቻለ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።
ባሕር ዳር: ግንቦት 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሐብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ
ኮሚቴ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርንና የተጠሪ ተቋማቱን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ገምግሟል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም 80 በመቶ መድረሱ በሕዝቡ ላይ መነቃቃት እንደሚፈጥር ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡
በግንባታው ሂደት የነበሩ የአፈጻጸም ችግሮችን በመፍታት 80 በመቶ መድረሱን በጥንካሬ ያነሱት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ
የተከበሩ ወይዘሮ ፈቲያ የሱፍ ሂደቱ ሕዝቡ ላይ የሞራል መነቃቃት የሚፈጥር ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በፋይናንስና በፐብሊክ ዲፕሎማሲውም ረገድ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸው የግንባታው አፈጻጸም ቀጣይነት እንዲኖረው
እንዳስቻለም ወይዘሮ ፈቲያ ገልጸዋል ፡፡
በተቋሙ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማስፋት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች አበረታች ቢሆኑም ከካሳ ክፍያና ከፍተኛ ኃይል
ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ብረቶች ስርቆት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከክልሎችና ከሕዝቡ ጋር በትብብር
መሥራት እንዳለበትም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢዋ አሳስበዋል፡፡
ለገጠር ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግና የኃይል ብክነትን መከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ በትኩረት
መሥራት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
በምግብ ራስን ለመቻልና ከውጭ የሚገባን ስንዴ ለማስቀረት የመስኖ ልማት ሥራዎችም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም
ጠቅሰዋል፡፡
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው የመስኖ ልማት ሥራዎችን አስመልክተው
በአሁኑ ወቅት ሥራ ላይ የሚገኙ አራት እንዲሁም አዳዲስ ወደ ሥራ የገቡ ስምንት በድምሩ 12 የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች
መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ16 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እንዲያገኝ መደረጉን
እንደገለጹ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m