
በሞጣ ከተማ አስተዳደር የተጠናቀቁ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ተመረቁ።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን የኹለት እጁ እነሴ ወረዳ ከ1947 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ የመንግሥት ተቋማት ለአገልግሎት በሚመች መልኩ በአዲስ ወደ አንድ ሕንፃ መጠቃለላቸው ለተሻለ አገልግሎት አሰጣጥ እንደሚያግዝ ተገልጿል።
የረጅም ዘመን የምሥረታ ታሪክ ያላት የሞጣ ከተማ ከከተማ አስተዳደርነቷ በተጨማሪ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች አንዱ የሆነው የኹለት እጁ እነሴ ወረዳ ዋና ከተማም ናት።
በሀገሪቱ የመንግሥት አስተዳደር መዋቅር ውስጥ ከአውራጃ እስከ ወረዳነት በተለያየ ዘመን ግልጋሎት የሰጠችው የሞጣ ከተማ በርካቶቹ የመንግሥት ተቋማት ቢሮዎች ከ1947 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት የሚሰጡ ነበሩ።
በኹለት እጁ እነሴ ወረዳ ከ2 ሺኅ 540 በላይ የመንግሥት ሠራተኞች በተለያዩ ዘርፎች ሕዝብን ያገለግላሉ። የወረዳው ተቋማት የተወሰኑት በኪራይ በርካቶቹ ደግሞ ምቹ ባልሆኑ ነባር ግንባታ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል። ይህንን ችግር ይቀርፋል የተባለለት እና 10 ተቋማትን የሚይዝ ሕንፃ በ40 ሚሊዮን ብር ግንባታው ተጠናቆ ተመርቋል።
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ተመሥገን ዘውዴ የቢሮ ችግሩ የሰፋ እና ስር የሰደደ ቢሆንም አሁን የተጠናቀቀው ግንባታ ችግሩን በመሠረታዊነት ይፈታዋል ብለዋል። በቀጣይም ለፍትሕ ተቋማት አገልግሎት የሚውል ሕንፃ ለመገንባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
በአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) እና በማኀበረሰቡ ተሳትፎ የተገነባ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ተመርቋል፡፡ በአንድ ባለሃብት የተገነባ ዘመናዊ ሆቴልም የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ አንድ አካል ነበር።
ከተቋማቱ የምረቃ ሥነ ሥርዓት በኋላ ከፌዴራል፣ ከክልል፣ ከዞን እና ከወረዳ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል። የወረዳዋ ማኅበረሰብ እና ተወላጅ ምሁራን በውይይቱ የከፍተኛ ትምሕርት ተቋም ግንባታ ጥያቄ የቆየ መሆኑን አንስተዋል። ለዚህም መንግሥት በአካባቢው ያሉ ወረዳዎችን ታሳቢ በማድረግ ጉዳዩን በትኩረት እንዲያየው ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው -ከሞጣ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4mቨ