ለፋሲል ከነማ ደማቅ አቀባበል ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡

149
ለፋሲል ከነማ ደማቅ አቀባበል ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የፋሲል ከነማ የባሕር ዳር አቀባበልን አስመልክቶ የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን እና የባሕር ዳር ከነማ ደጋፊዎች ማኅበር ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
አቶ አዱኛ ይግዛው የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነርና የፋሲል ከነማ የባሕር ዳር አቀባበል ዐቢይ ግብረ ሃይል ሰብሳቢ ፋሲል ከነማ ለዓመታት ሕዝብን ሲያስደስት የኖረ ክለብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት አቅሙን ያሳየባቸው እንደነበሩ አንስተዋል፡፡
“ክለቡ የባለፈው ዓመት ውድድር መቋረጥ ተፅዕኖ ሳያሳድርበት ጠንክሮ በመሥራት በ2013 ዓ.ም ለክልላችን ኩራት ሆናኗል” ሲሉ ተናግረዋል።
አቀባበሉን በተመለከተም ክለቡ በሦስት መንገድ አቀባበል እንዲደረግለት መወሰኑን ገልጸዋል።
ክለቡ አርብ ጠዋት ከ2:30 እስከ 3:00 ሰዓት ድረስ ባሕር ዳር ከተማ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል። በማርሽ ባንድ ታጅቦ የጎዳና ላይ ትዕይንት እንደሚኖርም አስታውቀዋል፡፡ አባላቱ ከአውሮፕላን ማረፊያ – ዲፖ – ኖክ – አዝዋ ሆቴል – ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን – ርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት – በድጋሚ ጊዮርጊስ እና ፓፒረስ አደባባይን ዙረው ማረፊያቸው አዲስ አምባ ሆቴል ይሆናል ተብሏል።
ምሽት ላይ ለክለቡ አባላት በአቫንቲ ሆቴል የእራት ግብዣ መዘጋጀቱም ተነግሯል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የዞን አስተዳዳሪዎች፣ የከተማ ከንቲባዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚታደሙ ተገልጿል።
በምሽቱ መርሃ ግብር ፋሲል ከነማን በገቢ ለማጠናከር በተያዘው ዕቅድ በባሕር ዳር እና ጎንደር ከተማ ላይ የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ በማሰብ ይገነባሉ የተባሉ የንግድ ማዕከላት ለሕዝብ ይፋ ይደረጋሉ ተብሏል።
የግንባታ ዕቅዶቹ ለሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች መቅረቡም ተጠቅሷል። እነዚህ ሥራዎች በአቀባበልና መስተንግዶ፣ በሃብት አሰባሰብ እንዲሁም በሚዲያና ኮምዩኒኬሽን ንዑሳን ግብረ ኀይሎች በቅንጅት እንደሚሠራ ተገልጿል።
ወጣት ዳንኤል በለጠ የባሕር ዳር ከነማ ደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዚዳንትና የፋሲል ከነማ አቀባበል ዐቢይ ኮሚቴ አባል የቡድኑ አባላት ወደ ባሕር ዳር ከመግባታቸው አስቀድሞ ከተማዋን በማስዋብ አቀባበሉን ለማድመቅ ሥራ መጀመራቸውን ገልጿል። ደጋፊዎችን በተለያየ መልኩ በመቀስቀስ ለአርብ ጠዋቱ መስተንግዶ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ የጣናው ሞገድ ደጋፊዎች ማኅበር ዝግጅት ማድረጋቸውን አሳውቋል።
ዘጋቢ፡- አማኑኤል ፀጋዬ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየሴቶች ኢንተርፕርነርሽፕ ፕሮጀክት የሴቶችን አቅም ለማጎልበት እድል መፍጠሩ ተገለጸ።
Next article“ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ስራ ፈጠራ የምትመች ሀገር ለመፍጠር በልዩ ትኩረት እየሠራ ነው” የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር