የሀሰት ሪፖርትን ለመከላከል ማዕከላዊ የመረጃ ቋት እያቋቋመ መሆኑን የግብርና ትራስፎርሜሽን ኤጄንሲ አስታወቀ፡፡

200

የሀሰት ሪፖርትን ለመከላከል ማዕከላዊ የመረጃ ቋት እያቋቋመ መሆኑን የግብርና ትራስፎርሜሽን ኤጄንሲ አስታወቀ፡፡

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲ በግብርናው ዘርፍ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ችግሮችን በመለዬት እና የመፍትሔ አማራጮችን በማስቀመጥ ግብርናን ለማዘመን እየሠራ ነው፡፡

ኤጄንሲው በክልል የሚስተዋለውን የሀሰት ሪፖርት ለመከላከል እና የመረጃ ቅብብሎሹን ዘመናዊ ለማድረግ በሙከራ ትግበራ ደረጃ ለተመረጡ ሦስት ወረዳዎች 68 “ታብሌቶችን” አስረከቧል፡፡

በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፕሮጀክት ኦፊሰር አቶ እንደሀገር ጌትነት እንደገለፁት ኤጄንሲው “ታብሌቶችን” ያስረከበው የመረጃ ቅብብሎሽን ከቀበሌ እስከ ፌዴራል መሥሪያ ቤት በማዕከላዊ የመረጃ ቋት (የሰርቨር ሲሰተም) ለማገናኘት ነው፡፡

ይህ አሠራር ከዚህ በፊት ዕቅዶች እና የሥራ ክንውን ሪፖርቶች በወረቀት ሲዘዋወሩ ከቀበሌ ወደ ወረዳ፣ ከወረዳ ወደ ዞን እና ክልሎች ወደ ፌዴራል ሲላክ ይፈጠር የነበርውን የሀሰት ሪፓርት ሙሉ በሙሉ እንደሚያስቀር ታምኖበታል፡፡ መረጃዎችም ከሚኒስቴር እስከ ቀበሌ የሚገናኙት በኔትወርክ ስለሚሆን በቀበሌ ባለሙያ ከተሠራው ሪፖርት ውጭ መረጃ መጨመርም ሆነ መቀነስ አያስችልም ነው የተባለው፡፡

65 “ታብሌቶች” ለቀበሌ ባለሙያዎች፣ ሦስት ታብሌቶች ደግሞ ለወረዳ ባለሙያዎች ተሰጥተዋል፡፡ “ታብሌቶቹ” የተሠራጩት በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲ አማካኝነት የጤፍ፣ የስንዴ እና የቢራ ገብስ ክላስተር ተብለው ለተመረጡ ቀበሌዎች ነው፡፡

በአማራ ክልል የግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ተቀባ ተባባል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ለሙከራ ትግበራ ያመጣቸው ታብሌቶች አስተማማኝ የመረጃ ሥርዓትን ለመዘርጋት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ መሆናቸውም ታውቋል፡፡ ክልል ቢሮ ተቀምጦ እስከ ቀበሌ ያሉ ችግሮችን በማዬት መፍትሔ ለማምጣት የሚያግዝ ቴክኖሎጂ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በቢሮው በመረጃ ቅብብሎሽ ሥርዓት አልፎ አልፎ የሀስት ሪፖርት እንደሚስተዋል ያመለከቱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው አዲሱ አሠራር ችግሩን ሙሉ በሙሉ ሊቀርፈው እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡

ቢሮው በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የተሰጡትን ታብሌቶች ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ የመከታተል፣ ሲበላሹ የመጠገን እና ለሥራው የሚመጥን ባለሙያ እንዲመደብ ይሠራል ነው የተባለው፡፡

የደጀን ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታሰው ሞኝሆዴ ‹‹በግበርና ላይ የሚሠራው ሥራ መረጃ ላይ የተደገፈ አልነበረም፤ አሁን ግን በተሰጡን ታብሌቶች መረጃዎችን በፎቶ ግራፍ አስደግፈን እንልካለን›› ብለዋል፡፡ በወረቀት ብቻ ተወስኖ የነበረውን የመረጃ ቅብብሎሽ ሥርዓት በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡ በሙከራ ትግበራ ደረጃ የተመረጡ ወረዳዎች አዋበል፣ ደጀን፣ ሞረት እና ጅሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

Previous articleበአማራ ክልል አርሶ አደሩን መሠረት ያደረገ የገንዘብ ቁጠባ ፌደሬሽን ሊመሠረት ነው፡፡
Next articleፈረንሳይ ላልይበላን የመጠገን ቃሏን ልትተገብር ነው፡፡