
የሴቶች ኢንተርፕርነርሽፕ ፕሮጀክት የሴቶችን አቅም ለማጎልበት እድል መፍጠሩ ተገለጸ።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ሁለተኛው የሴቶች ኢንተርፕርነርሽፕ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ ሴት ኢንተርፕርነሮች እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
በዓለም ባንክ የሚደግፈው ይህ ፕሮጀክት በመጀመሪያው ምዕራፍ ላለፉት ሰባት ዓመታት ሲተገበር መልካም ውጤት እንደተገኘበት ተገልጿል፡፡
ያለፉ የተግባር ሂደቶችን በመገምገም ሁለተኛው ምዕራፍ ሊጀመር መርሃ ግብሩ በመካሄድ ላይ ይገኛል። በመርሃ ግብሩ “የስኬት መንገድ” በተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ላይ ሃሳብ የሰጡ ሴት ኢንተርፕርነሮች በፕሮጀክቱ ሕይወታቸው እንደተለወጠ ገልጸዋል፡፡
የሴቶች የብድር አመላለስ ሲታይ 99 በመቶ መሆኑን የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ገብረመስቀል ጫላ ገልጸዋል። ይህንን በማየትም የዓለም ባንክ ለሁለተኛው ምዕራፍ 100 ሚሊዮን ዶላር የረጅም ጊዜ ብድር ማመቻቸቱን አስታውቀዋል፡፡
የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር ዲኤታ ያስሚን ወሃረቢ በተለያየ ዘርፍ የሴቶች ዕድል የጠበበ ቢሆንም በታዳጊ ሀገራት የባሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያም በበርካታ ተግባራት ሴቶች ውስን እድል ያላቸው በመሆኑ በገንዘብ የማጠንከር ተግባሩ ግድ ስለሆነ ከአጋር የገንዘብ ተቋማት ጋር በመሆን ፕሮጀክቱ መጀመሩን ነው የተናገሩት፡፡
ዛሬ በይፋ የሚተዋወቀው ሁለተኛው ምዕራፍ በአግባቡ እንዲተገበር እንደሚሠሩም አስታውቀዋል።
የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ “ሴቶች ከተደገፉ አቅማቸው ምን ያህል እንደሆነና የጽናት ተምሳሌትነታቸውን ያየንበት ፕሮጀክት ነው” ብለዋል። ከቡና መሸጥ እስከ ግዙፍ ሕንጻ መገንባት፣ ከኮፒ ማሽን ሠራተኝነት እስከ ማተሚያ ድርጅት እንዲሁም መሰል የጽናት ሥራዎች መታየታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል። በዚህም ከዓለም ባንክ ሦስት ሽልማቶች እንደተበረከተ አንስተዋል፡፡ ትውልድን የሚቀርጹ እናቶችን አቅም ማጠንከር ትውልድን ማነጽ ነውም ብለዋል ሚኒስትሯ አይሻ መሃመድ።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ “በዚህ የተግባር ሂደት ውስጥ ያላችሁ ሴቶች ራሳችሁን ከመለወጥ ባሻገር በማኅበረሰቡ ውስጥ ተንሰራፍቶ ያለውን የሴቶች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ቀርፋችኋልና ምሥጋና ይገባችኋል” ብለዋል።
ፕሬዚዳንቷ የመጀመሪያው ምዕራፍ ያለፉት ሰባት ዓመታት በስኬት መጠናቀቁን እና ለቀጣይም በትጋት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው አባቡ–ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ