ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቁን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

224
ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቁን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በቀጣዩ የክረምት ወራት ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ተወካይ ዳይሬክተር እስመለዓለም ምህረት ነግረውናል፡፡ እስካሁንም ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል ብለዋል፡፡ አቶ እስመለዓለም እንዳሉት ችግኞቹ በግለሠብ፣ በማኅበራት፣ በተቋማት፣ በፕሮጀክቶች እና በመንግሥት የችግኝ ጣቢያዎች እየተፈሉ ናቸው፡፡ እንደ ቢሮው መረጃ:
• ከ1 ሚሊዮን 800 ሽህ በላይ ችግኞችን ለማፍላት እቅድ ተይዟል።
• ከ1 ሚሊዮን 350 ሽህ በላይ ችግኞች በተለያዩ የችግኝ ጣቢያዎች ተፈልተው ለተከላ ዝግጁ ሆነዋል።
• ችግኞቹ 181 ሽህ 176 ሄክታር መሬት ላይ ይተከላሉ።
• እስካሁን ከተፈሉት ችግኞች ውስጥ 182 ሚሊዮኑ ሀገር በቀል ናቸው።
•የክልሉን የደን ሽፋንም በ1 ነጥብ 5 በመቶ ያሳድገዋል።
•በችግኝ ከሚሸፈነው መሬት ውስጥ 35 ሺህ ሄክታር መሬት ተለይቶ ካርታ ተሠርቶለታል። አቶ እስመለዓለም የተፈሉ ችግኞች የማኅበረሰቡን የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጡና ምርታማነትን የሚያሳድጉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳሉት ዋንዛ፣ የሀበሻ ጽድ እና መሰል ሀገር በቀል ችግኞች በብዛት እየለሙ ሲሆን ዲከረንስ፣ ባሕር ዛፍ እና የውጭ ዝርያ ያላቸው ችግኞችም ይገኙበታል፡፡ የሚለሙ ችግኞች ለደን ልማት፣ ለጥምር ደን እና ተፋሰሶችን በሥነ-ሕይወታዊ ዘዴ ለማከም ተብለው እንደሚለዩም ተናግረዋል፡፡
የሚተከሉ ችግኞች ፈጥነው በመድረስ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው የጎላ እና የአርሶ አደሮችን የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል፡፡ እንደ አቶ እስመለዓለም ገለጻ ችግኞቹ የአፈር ክለትን በመቀነስ የሠብል ልማትን፣ የእንስሳት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እድገትን ማምጣት የሚችሉ ናቸው፡፡ ለችግኝ ተብለው በተለዩ ቦታዎች፣ በእርሻ ማሳዎች፣ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ በተከናወነባቸው ቦታዎች የሚተከሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
አቶ እስመለዓለም አርሶ አደሮች ለተከላ የተለዩ ቦታዎችን ዝግጁ በማድረግና የሚቀርቡ ችግኞችን በተገቢው መንገድ መትከል አለባቸው ብለዋል፡፡ የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ሥራውም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት፡፡
በ2012 ዓ.ም በክርምት ወራት ከተተከሉ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች ውስጥ 78 በመቶ ያህሉ መጽደቃቸውን ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡
ዘጋቢ ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleከመተከል ዞን የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመመለስ የአካባቢ ልየታ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑ ተገለጸ፡፡
Next article“ከሞጣ ሌላ ምን ይምጣ”