
ከመተከል ዞን የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመመለስ የአካባቢ ልየታ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑ ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥታት፣ የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኀይል፣ የሰላም ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ብሔራዊ አደጋ ስጋት የሥራ ኀላፊዎች ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ ከሰሞኑ ከተፈናቃይ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል፡፡
ተፈናቃዮችን በልዩ ሁኔታ ወደ መተከል ዞን ለመመለስ አራት ጊዜያዊ ማዕከላት መለየታቸውን የሰላም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ከሁለቱ ክልል መንግሥታት፣ ከመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኀይል፣ ከሰላም ሚኒስቴርና ከብሔራዊ አደጋ ስጋት የተውጣጡ አካላት እንዲሁም መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ቦታዎቹን በቂ እና ምቹ መኸናቸውን የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡
ቅድሚያ ቻግኒ በሚገኘው ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ያሉ ከ29 ሺህ በላይ ተፈናቃዮችን ለመመለስ እንደታሰበ በሚኒስቴሩ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ይትባረክ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡ በሂደት በአዊ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችን የመመለስ ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል፡፡
ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው ለማጓጓዝ የሚያስፈልግ ገንዘብ እንዲሟላ ለገንዘብ ሚኒስቴር ጥያቄ መቅረቡንም አመላክዋል።
አስፈላጊው ገንዘብ እንደተገኘም በቀጥታ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
የአካባቢውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሁለቱ ክልል መንግሥታት የጋራ የሰላምና የልማት ግብረ ኀይል አቋቁመዋል፡፡ በጸጥታ እና በልማት ጉዳዮች በጋራ የሚሠራው ግብረ ኀይሉ የምዕራብ እዝ ምክትል አዛዥን፣ የዞኑን ዋና አስተዳዳሪና ከሁለቱ ክልሎች የተውጣጡ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችን የያዘ ነው፡፡
ከሁለቱም ክልሎች የሰው ኀይል የተመደበ ሲኾን የጽሕፈት ቤቱ መቀመጫ ግልገል በለስ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ በቅርቡ መደበኛ ሥራ እንደሚጀምር የጠቀሰው የጋራ ግብረ ኀይሉ በጋራ በጀት የሚያዝለት፣ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች የሚያግዙትና የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ የሚያደርግለት ነው፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳሉት የኮሚቴው መቋቋም የሁለቱን ክልሎች ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጠርና ልማት እንዲፋጠን ምቹ መደላድል ይፈጥራል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ