“ለስፖርቱ ዘርፍ ትኩረት በመስጠት ለሰላም፣ ለአብሮነትና ለወንድማማችነት ማጠናከሪያ ገመድ ሆኖ እንዲያገለግል መሥራት ይገባል” የጎንደር ከተማ ከንቲባ

156
“ለስፖርቱ ዘርፍ ትኩረት በመስጠት ለሰላም፣ ለአብሮነትና ለወንድማማችነት ማጠናከሪያ ገመድ ሆኖ እንዲያገለግል መሥራት ይገባል” የጎንደር ከተማ ከንቲባ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) “ስፓርት ለኢትዮጵያ ህብረት “በሚል መሪ መልዕክት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ የሆነውን የፋሲል ከነማ የእግር ኳስ ክለብ ለማጠናከር የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በመርሃ ግብሩ ላይ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሞላ መልካሙ እንዳሉት ስፓርት ጠንካራ ሀገራዊ ህብረትን፣ አንድነትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን እና ሁለንተናዊ እድገትን ለማጠናከር ሚናው የጎላ ነው።
በተለይ የእግር ኳስ ስፖርት በሀገር መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ በሚከናወኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ክንውኖችን በማጠናከር ጠቀሜታው ከፍተኛ በመሆኑ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል።
በቀጣይም ለስፖርቱ ዘርፍ ትኩረት በመስጠት ለሰላም፣ ለአብሮነትና ለወንድማማችነት ማጠናከሪያ ገመድ ሆም እንዲያገለግል መሥራት እንደሚገባ አንስተዋል።
ክለቡ በሀገሪቱ የመናገር ነፃነት ባልነበረበት ወቅት ለሁሉም የተገፉ ዜጎች የነፃነት ድምፅ በመሆን ማገልገሉንም ገልጸዋል።
ፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ከሁሉም አካባቢዎች የመጡ ተጨዋቾችን ያካተተ በመሆኑ የትንሿ ኢትዮጵያ ተምሳሌት ነውም ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራች ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ እግር ኳስ መሥራችም በመሆኗ የሀገሪቱን እግር ኳስ በአፍሪካ መድረክ ከፍ ለማድረግ ክለቡን መደገፍ እንደሚገባ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ክለቡ አሁን ካለበት ደረጃ እንዲደርስ ሌሎች ድርጅቶች ከሚያድጉት ድጋፍ በተጨማሪ ከተማ አስተዳደሩ ከበጀቱ 5 በመቶ የሚሆነውን ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።
ቋሚ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው ነባሩን ስታዲዮም ለማደስ እና የእግር ኳስ አካዳሚ ለመግንባት በሚደረገው ሂደት በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዲያደርጉም ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል።
የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግበሩ ግንቦት 20 ባህርዳር፣ ግንቦት 21 ደግሞ በጎንደር ከተማ እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።
በዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ፋሲል ከነማን ማጠናከር የኢትዮጵያን ስፖርት ማጠናከር ነው” የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር
Next articleፋሲል ከነማን መደገፍ የጋራ ጀግናን የማሳደግ፣ የማሻገር ተግባራዊ ምላሽ መሆኑን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡