ዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ዩናይትድ ኪንግደም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነት እየተጠናከረ እንዲሄድ የመንግሥታቸውን ድጋፍ ገለጹ።

119
ዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ዩናይትድ ኪንግደም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነት እየተጠናከረ እንዲሄድ የመንግሥታቸውን ድጋፍ ገለጹ።
ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በዩናይትድ ኪንግደም የኢፌዲሪ ልዩ መልእክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ተፈሪ መለሰ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለዩናይትድ ኪንግደም ዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ አቅርበዋል፡፡
አምባሳደሩ የሹመት ደብዳቤያቸውን ባቀረቡበት ወቅት በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን ልዑል ፊሊፕ በማስመልከት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።
ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የቆየው የኢትዮጵያና የዩናይትድ ኪንግደም ግንኙነትን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገርና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ለማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚሠሩ ለዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ገልጸዋል፡፡
ዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ ጠንካራ የልማት አጋር መሆኗን የጠቀሱት አምባሳደሩ የልማት ድጋፉ የበርካታ ዜጎችን ህይወት ለመለወጥ ያስቻለ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ አዲስና መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ የሪፎርም ሂደት ላይ እንደምትገኝና የመልካም አስተዳደር ፣ የኢኮኖሚና የዲሞክራሲ እድገትን ለማምጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አምባሳደሩ አስገንዝበዋል። የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋ አመላክተዋል፡፡
አምባሳደር ተፈሪ በቅርቡ በግላስጐ በሚካሄደው የCop 26 የአየር ንብረት ጉባዔ የተሳካ እንዲሆን ኢትዮጵያ አበክራ እንደምትሠራ ጠቁመዋል። በዚህ ረገድ መንግሥት የጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ ፕሮጀክት ለማሳካት በዚህ ዓመት 6 ቢሊየን ዛፎች በመትከል እንዲሁም አንድ ቢሊዮን ችግኞችን ለጎረቤት ሀገሮች በማከፋፈል የአካባቢ ንብረት ተጽዕኖን ለመቋቋም በትኩረት እየሠራች መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ግዴታዎችን እንደምትወጣም ተናግረዋል።
ዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ በበኩላቸው በንጉሥ ኃይለሥላሴ ዘመን በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት አስታውሰዋል።
ከኢትዮጵያ ጋር ያለው የቆየ ግንኙነት እየተጠናከረ እንዲሄድ የመንግሥታቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዩናይትድ ኪንግደም ኤምባሲዋን በመክፈት ቀዳሚዋ አፍሪካዊት ሀገር እንደሆነች በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያደረሰን መረጃ ያመላክታል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleለምርት እድገትና ለማኅበረሰብ ጤና መጠበቅ ፀረ-ተባይ ኬሚካልን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ የግብርና ሚንስቴር አስታወቀ፡፡
Next article“ፋሲል ከነማን ማጠናከር የኢትዮጵያን ስፖርት ማጠናከር ነው” የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር