ለምርት እድገትና ለማኅበረሰብ ጤና መጠበቅ ፀረ-ተባይ ኬሚካልን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ የግብርና ሚንስቴር አስታወቀ፡፡

422

ለምርት እድገትና ለማኅበረሰብ ጤና መጠበቅ ፀረ-ተባይ ኬሚካልን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ የግብርና ሚንስቴር
አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ላየንስ ዓለም ዓቀፍ የሰብል ጥበቃ እና የፀረ-ተባይ ኬሚካል አቅራቢ ድርጅት
ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሰብል ጥበቃና ፀረ-ተባይ ኬሚካል አጠቃቀም ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በባሕር ዳር
ውይይት አካሂዷል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ግብዓት አቅርቦት ዳይሬክተር መንግሥቱ ተስፋ በአርሶ አደሮች ዘንድ የሚታየው የኬሚካል
አጠቃቀም ችግር መስተካከል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ አቶ መንግሥቱ አርሶ አደሮች ፀረ-አረም ኬሚካል በሚጠቀሙበት ወቅት
መጠኑን፣ የሚጠቀሙበትን ሰዓት እና መልበስ ያለባቸውን አልባሳት ማወቅ አለባቸው ብለዋል፡፡
ተገቢውን ጥንቃቄ ሳያደርጉ ርጭት ማካሄድ ምርት ከመቀነሱ ባሻገር ለተለያዩ በሽታዎች ያጋልጣል ነው ያሉት፡፡ ለአንድ ማሳ
እንዲጠቀም ከተቀመጠው መጠን ያነሠ ወይም የበዛ ከተጠቀመ በምርታማነቱ ላይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡ የኬሚካል
መያዣ እቃዎችም ሆኑ የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው ኬሚካሎች በሀገር ውስጥ የሚወገዱበት ሥርዓት አለመኖር ችግሩን
እንዳባባሰው ተናግረዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ የኬሚካል እቃዎችን ለሌላ ነገር አገልግሎት እንዳይውሉ በአግባቡ ማስወገድ
እንደሚገባ መክረዋል፡፡ የአጠቃቀም ችግሩን ለመቅረፍ በክልል ደረጃ የተዘጋጁ የአንድ ማዕከል የግብርና ግብዓት አቅርቦትና
አገልግሎት ማሳደጊያ ማዕከላት ላይ የሚደረገው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አበባው ጌቴ ምርትን ለማሳደግ ኬሚካሎችን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አቶ አበባው እንዳሉት ኬሚካሎች በአግባቡ ካልተያዙ በሰዎች፣ በእንስሳትና በሰብሎች ላይ ጉዳት ያደርሳሉ፤ ችግሩን
ለመቅረፍም በክልሉ ለሚገኙ ባለሙያዎች ሥልጠና ተሠጥቷል ነው ያሉት፡፡
አቶ አበባው አርሶ አደሩ ግንዛቤው በማደጉ ከተመረጡ ቦታዎች ገዝቶ መጠቀም ጀምሯል ብለዋል፡፡ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር
የሚሠሩ የልማት ፕሮጀክቶች ሠርቶ ማሳያ ጣቢያዎች ላይ ሙከራ በመሥራት የአርሶ አደሩን ግንዛቤ እያሳደጉ መሆኑንም
ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በየዓመቱ ይፈጠር የነበረውን የኬሚካል እጥረት ለመቅረፍም ግዥ በመፈጸሙ በዚህ ዓመት የኬሚካል ችግር
እንደማይኖር ጠቅሰዋል፡፡
የላየንስ ዓለም ዓቀፍ የሰብል ጥበቃ እና ፀረ-ኬሚካል አቅራቢ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ውብእሸት ዓለሙ በድርጅታቸው በኩል
የሚገቡ ኬሚካሎች ወደ ሀገር ሲገቡ በሰው፣ በእንስሳት እና በአካባቢ ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ
እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አቶ ውብእሸት “የምናስመጣቸው ኬሚካሎች ችግር ፈቺ መሆናቸውን በገበሬ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ላይ
የሙከራ ሥራ በመስራት እያሳየን ነው” ብለዋል፡፡
አርሶ አደሮች በፈቃደኝነት እንዲገዙ ለማድረግ እየሠሩ ቢሆንም አንዳንድ አርሶ አደሮች በሕገ ወጥ መንገድ የሚገባውን ኬሚካል
እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል፡፡ ይህም በምርት ላይ የሚያስከትልው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ እናም ሕጋዊ ግዢ ብቻ እንዲፈጸም
መክረዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የግብርና ሚኒስቴርና የክልል የሥራ ኀላፊዎች፣ አቅራቢ ድርጅቶች፣ ዩኔኖች፣ የአንድ ማዕከል የግብዓት እቅርቦት
አገልግሎት ኀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈውበታል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“የተዘጋጀልን ጥፋት የከፋ፣ ያጋጠመን ችግር ከባድ ቢሆንም ከአብሮነታችን በታች ነበርና በትዕግስት አልፈነዋል” አሚኮ ያነጋገራቸው የሞጣ ከተማ ወጣቶች
Next articleዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ዩናይትድ ኪንግደም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነት እየተጠናከረ እንዲሄድ የመንግሥታቸውን ድጋፍ ገለጹ።