“የተዘጋጀልን ጥፋት የከፋ፣ ያጋጠመን ችግር ከባድ ቢሆንም ከአብሮነታችን በታች ነበርና በትዕግስት አልፈነዋል” አሚኮ ያነጋገራቸው የሞጣ ከተማ ወጣቶች

104
“የተዘጋጀልን ጥፋት የከፋ፣ ያጋጠመን ችግር ከባድ ቢሆንም ከአብሮነታችን በታች ነበርና በትዕግስት አልፈነዋል” አሚኮ ያነጋገራቸው የሞጣ ከተማ ወጣቶች
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሦስቱ እነሴዎች ማእከል እና የሕብረ ቀለም ጌጥ እንደሆነች ይነገራል፤ ሞጣ ከተማ። እድሜ ጠገቧ ከተማ ከባሕላዊው እስከ ዘመናዊው ትምሕርት “የቀለም ቀንድ እናት ናት” ይሏታል። ከአራት ዓይና እስከ ኡላማ ሞጣን አንቱ ያስባሏት ሊቆች ብዙዎች ናቸው። ከምንም በላይ ደግሞ ሞጣ የመቻቻል እና የአብሮነት ከተማነቷን የሚመሰክሩ ሁሉ እምባ ከዓይናቸው፣ ስሜት ከደም ስራቸው ጎልቶ ይነበባል። ግጭት ጠማቂዎች “ከቀን ክፉ አንድ ቀን አብሮነትን ይጎዳል፣ ሕብረትን ይንዳል እንዲሁም አለመተማመንን ይወልዳል” ያሉትን ሴራ በዚች የሕብር ከተማ ለመፈፀም ሞከሩ።
ታኅሣሥ 10/2012 ዓ.ም በዚች የመቻቻል ከተማ የእምነት ተቋማት ተጎዱ፤ የንግድ ድርጅቶችም ነደዱ። ድርጊቱ ስሜታዊ ያደረገው የሞጣ ከተማን ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን ከእሴቱ ያፈነገጠ ድርጊት ያየውን እና የሰማውን የአማራ ሕዝብ ጭምር ነበር። ያንን ፈታኝ ወቅት በጽናት እና በትዕግስት ያሳለፉት የሞጣ ከተማ ነዋሪዎች በመጭው ሐሙስ “ሕብር እና ፍቅር በሰባቱ ዋርካ” በሚል መሪ መልዕክት በፈተናቸው ወቅት ከጎናቸው የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ያመሰግናሉ፤ ሰላማቸውን፣ ፍቅራቸውን፣ አንድነታቸውን እና ወንድማማችነታቸውን ዳግም ሊያድሱ ቀነ ቀጠሮ ይዘዋል።
ከአብሮነት ቀን ቀድመው ዛሬ ደግሞ “በፍቅር እንኖራለን፤ በአንድነትም እንሻገራለን” በሚል መሪ መልዕክት የእርቀ ሰላም ማደማደሚያ ተካሂዷል። የበደለ ክሶ፣ ያጠፋ መልሶ እርቅ በሚመሰረትባት ኢትዮጵያ ስህተቶችን አርቀው ለመጭው ተጠንቅቀው በአብሮነት ለመኖሩ “ይቅር ስለፈጣሪ” ተባብለዋል።
ከመርኃ ግብሩ መጠናቀቅ በኋላ አሚኮ ያነጋገራቸው ወጣቶች “የተዘጋጀልን ጥፋት የከፋ፤ ያጋጠመን ችግር ከባድ ቢሆንም ከአብሮነታችን በታች ነበርና በትዕግስት አልፈነዋል” ብለዋል።
የሞጣ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት እሱያውቃል ተመስገን ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ ምንጩን ለማጣራት የከተማዋ ወጣቶች ረጅም ርቀት መጓዛቸውን ጠቅሷል፡፡ “የተለየ አጀንዳ እና ዓላማ የተሰጣቸው አካላት በመካከላችን ገብተዋል” ይላል በልጅነት ዘመኑ ያሳለፈውን ሕብረት አስታውሶ።
ሌላው አስተያየት ሰጭ ወጣት አብዱልከሪም ኑርሁሴን ክርስቲያን እና ሙስሊም ከበዓላት እስከ ማኅበራዊ ሕይዎት በአብሮነት ማሳለፍ በሞጣ የተለመደ ነው ብሏል። ባይሳካላቸውም የተፈጠረው ችግር ይህንን አብሮነት ጥርጣሬ ውስጥ ለመክተት ያለመ እንደነበር በመግለጽ፡፡
አብዱልከሪም የተለየ አጀንዳ ያላቸውን አካላት ቀድሞ መለየት እና ማረም ያስፈልጋል ነው ያለው። በተለይም ከሃይማኖት ተቋማት እና አባቶች ብዙ ይጠበቃል ብሏል። ወጣቶችም ከተማቸው ቀድሞ ወደምትታወቅበት የመቻቻል እና የአብሮነት እሴት እንድትመለስ ወጣቶች ከጸጥታ ኃይል እና ከመንግሥት ጋር በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ታዘብ አራጋው -ከሞጣ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article‹‹አሁንም በመርዛማ ወሬያችሁ ልታንበረክኩን አትችሉም። ይህንም ታሪክ እንደ ዓደዋው ድል ዳግም ዓደዋ ተብሎ እንደሚወሳ እርግጠኞች ነን›› ኮሎኔል ጌትነት አዳነ
Next articleለምርት እድገትና ለማኅበረሰብ ጤና መጠበቅ ፀረ-ተባይ ኬሚካልን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ የግብርና ሚንስቴር አስታወቀ፡፡