
‹‹አሁንም በመርዛማ ወሬያችሁ ልታንበረክኩን አትችሉም። ይህንም ታሪክ እንደ ዓደዋው ድል ዳግም ዓደዋ ተብሎ እንደሚወሳ እርግጠኞች ነን›› ኮሎኔል ጌትነት አዳነ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ሲገጥሟት ታሸንፋቸዋለች፣ ዝም ስትላቸው ታስፈራቸዋለች፣ ዝምተዋ ያስፈራል፤ ጠቧ ይሰባብራል፣ ፍቅሯ ደግሞ አንጄት ያርሳል፡፡ ሀገራት ታሪኳ፣ ጀግንነቷና አይሸነፌነቷ ሰላም ሰጥቶ አያስተኛቸውም፡፡ ዝቅ ብሎ ማደር፣ ጠላትን ከወሰን ወዲህ ማሻገር የማትወደው ኢትዮጵያ ሚስጥር የሆነው ታሪኳ ሀገራትን ያስጨነቃቸው ይመስላል፡፡ ተውኝ ስታለችው አይተዋት፣ ሲገጥሟት አይችሏት፣ ችግር የሆነባቸው ይመስላል፡፡
ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች እንጂ፣ ወደኃያላን ነን ባዮች ትዘረጋለች አለመባሉን የረሱም ይመስላሉ፡፡ ለፍቅር እንጂ፣ ለመደፈር እጅ እንደማትሰጥ፣ እጅ እንደማትነሳም ታሪኳን ያወቁ አይመስሉም፡፡
የነጭን ተስፋና ምኞት በአፍሪካ ምድር ያከተመችው ኢትዮጵያ መከራዎች ቢበዙባታም ዘመን ለመሻገር ያገዳት አልነበረም፡፡
በዓድዋ ተራራ ላይ ያበራችው የድል ጮራ ምድረ አፍሪካን አብሮቶ ነጭን ጠራርጎ ሲያስወጣ የጠላት ዓይኖች ኢትዮጵያ ላይ አረፉ፡፡ አፍሪካን የስቃይ ምድር እንዳትሆን ያደረገችው ኢትዮጵያ ለቀኝ ገዢዎች መጥፎ ተምሳሌት ናት፡፡ የጨለመውን አብራተለች፣ ተስፋ ላጣው ተስፋ ሆናለች፣ የዘገዬውን አፍጥናለች፣ የከበደውን አቅልላለች፣ የማይሸነፍ የሚመስለውን አሸንፋለች ኢትዮጵያ፡፡
ኢትዮጵያዊ ለሀገሩና ለክብሩ ሲል ሞትን ይንቃል፣ የመከራውን ዘመን በድል ይሻገራል፣ የኢትዮጵያ ክብር ከሚደፈር፣ እኔ ቀድሜ ወደ አፈር ይላል፡፡ ኢትዮጵያ ከምንም በላይ ናትና፡፡ ኢትዮጵያን በክፉ ዓይን የሚመለከቷት አሁንም ዓይናቸውን አላነሱም፡፡ ዘመን እየጠበቁ አሁንም መመልከት ላይ ናቸው፡፡
የአሸባሪውን ሕወሃት መደምሰስ ተከትሎ ሀገራት ስለ ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃሳቦችን እየሰጡ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን እውነት የሚደግፉና፣ የሚነቅፉ ሀገራት እየታዩ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ሉዓላዊነቴን አላስደፍርም እንጂ ያለውን እውነት ግን እወቁ፣ ስለ እውነትም እውነተኛ ፍርድ ስጡ እያለች ነው፡፡
በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል በተወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ማግሥት ክልሉን መልሶ ለማቋቋም በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን መንግሥት በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡ ድጋፉም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እየገለፀ ይገኛል፡፡
ይሁን እንጂ አንዳንድ ሀገራት ኢትዮጵያ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ያልተገባ ነገር አድርጋች፣ የሰበዓዊ ድጋፍ እየተደረገ አይደለም፣ ዜጎች ላይ ግፍ እየተፈፀመ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
በትግራይ ክልል የተወሰደው የሕግ ማስበር ዘመቻ ካልተዋጠላቸው ሀገራት መካከል አሜሪካ አንዷ ናት፡፡ እርሷም ለሕዝብ ያዘነች ሳይሆን ለራሷ ጥቅም የቆመች ናት እየተባለ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ላይ ተጠቅመዋች ስለተባለችው ያልተገባ ነገር የመከላከያ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ መልስ ሰጥተዋል፡፡
የመርዛማ ጋዝ ጦር መሳሪያን መጠቀም እልቂቱንና ጉዳቱን ወራሪ ቅኝ ገዥዎች በጀግኖች አያት ቅደመ አያቶቻችን ላይ በፈፀሙት ጥቃት አሳምረን እናውቀዋለን ብለዋል፡፡
የኢፌድሪ መካከያ ሠራዊት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ተፈፀመ ተብሎ የሚዘገበው የመርዛማ ጋዝ ጥቃት ሊሆን ቀርቶ ሊታሰብ የማይችል ነው ብለዋል ፡፡ ውሸት የማያልቅበት አሸባሪው ህወሃት አሁንም በሃሰት ማደናገሩን ቢቀጥልም፣ በተለይ ቀደም ብሎ ውሸት ይፈበረክ እንደነበር ብዙ ማሳያዋች እንዳሉ አስረድተዋል።
ʺየኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የትግራይ ሕዝብን እየጨፈጨፈ ነው፣ ሴቶች ተደፈሩ ፣ ሬሳ ገደል አስገቡ፣ እርዳታ ተከለከለ፣ ገበሬው እርሻ እንዳያርስ ተደረገ፣ ንብረቱ ወደመና ተዘረፈ አልፎም የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞች ታገቱና ተገደሉ ” እያሉ ራሳቸው የፈፅሙትን ድርጊት አስመስለው በመቅረፅ ጭምር ሲያሰራጩ ቆይተዋል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ።
“ጅብ ከማያውቁት ሀገር……….” እንዲሉ 27 ዓመት የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲያታልልበት የነበረው ፕሮፖጋንዳ በሀገር ውስጥ ሲጋለጥና ሲከሽፍ፤ ለማያውቁት፣ ቢያውቁትም በጥልቀት ላልተረዱት ወይም ለተገዙት” ጅቡ የተነጠፈለትን አጎዛ እስኪበላ ድረስ” እንግዳ ብለው እነሱ ያስተናግዱት እንጂ እኛ ከበቂ በላይ እናውቀዋለን ብለዋል ኮሎኔሉ።
ይህን አይነት የበሬ ወለደ ውሸት የሚያስተናግዱ ሚዲያዎችና ግለሰቦች አንድም ለቆየ ዓላማቸው፤ በሌላም ኢትዮጵያ በተዘረፈችው ዶላር የተገዙ ነጭ ሸብር ፈጣሪዎች መሆናቸውንም አስረድተዋል ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ግን የውጭ ወራሪዎች በቀደምት አያት ቅድመ አያቶቻችን ላይ የተፈፀመውን ግፍና መከራ ጠንቅቀን ስለምናውቅ ፣ እንኳን በዜጎቻችን በማንኛውም ፍጡር ላይ መጠቀም እንደማንችል ሕጉ ብቻ ሳይሆን ሞራላችን እንደማይፈቅድ ሊታወቅ ይገባል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የጅምላ ጨራሽ ጦር መሳሪያዎችን ያለመጠቀምና ያለማስተላለፍ ዓለም አቀፍ ስምምነትን የፈረመች እና ያፀደቀች ቀዳሚ ሀገር ናት ። በወራሪዎችም የጥቃቱ ሰለባ እንደነበርን እንዲህ ሲነካካ ያስታውሳል ነው ያሉት ።
የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ʺበአያት ቅደመ አያቶቻችን በደረሰ መርዛማ ጋዝ ያልተንበረከክን የወላጆቻችን ተተኪ ልጆች ነን። አሁንም በመርዛማ ወሬያችሁ ልታንበረክኩን አትችሉም። ይህንንም ታሪክ እንደ ዓደዋው ድል ዳግም ዓደዋ ተብሎ እንደሚወሳ እርግጠኞች ነን” ብለዋል።
የአሁኑ መርዛማ ጋዝ፣ የውጭው ወሬና ጫና መሆኑ ታውቆ፤ በአንዳንድ ቅጥረኛ ሚዲያ የሚሰራጭ ዘመቻን በተገቢው ልክ ስለምንረዳ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንደ ቀደሙት አያት ቅደመ አያቶቻችን ጠብቀን እኛም ለመጭው ትውልድ ጀግንነትን እናወርሳለን ነው ያሉት ኮሎኔል ጌትነት አዳነ።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ