የተሻለ የጥጥ ምርት በማምረት ያጋጠመውን የግብዓት እጥረት ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

183
የተሻለ የጥጥ ምርት በማምረት ያጋጠመውን የግብዓት እጥረት ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ለጥጥ ልማት አመቺ የሆነ ወደ 3 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ ለም መሬት ያላት መሆኑን የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል። ኢንስቲትዩቱ ለጥጥ ምርት ተስማሚ በሆኑ አካባቢዎች ያለውን አቅም በመጠቀም እየጨመረ የመጣውን የጥጥ ፍላጎት ለማሟላትና የዘርፉን አቅም ለመጠቀም እየሠራ መሆኑን ገልጿል፡፡
በፀጥታ ችግር ፣ የግብአት አቅርቦት፣ የመሬት እና የመሠረተ ልማት ችግሮች ምክንያት በዘርፉ ለተሠማሩ ፋብሪካዎች የሚሆን የጥጥ አቅርቦት ችግር መከሠቱን አስታውቋል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በ2013/14 የምርት ዘመን እጥረቱን ሊያካክሱ ይችላሉ ተብለው በተለዩ አካባቢዎች የምርት ንቅናቄ መድረክ መጀመሩን የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የጥጥ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሰለ መኩሪያ ገልጸዋል፡፡ በጉዳዩ ላይም የፌዴራል፣ የክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና የዘርፉ አልሚዎች በተገኙበት የንቅናቄ መድረክ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።
በውይይቱ በዘርፉ የተሰማሩና ለመሰማራት ፍላጎቱ ያላቸውን የጥጥ አልሚዎች በሀገሪቱ ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም የግብዓት ፍላጎትን ለማሟላት የተደራጀ እንቅስቃሴን በማድረግ በ2013/14 የምርት ዘመን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ አልሚዎች ያሉባቸውን የግብዓት አቅርቦት እጥረት፣ የመሰረተ ልማት እና የግብይት ችግሮች በቅንጅት በመፍታት ትኩረት ይደረጋል ተብሏል።
ባለፉት ዓመታት የነበረውን ልምድ በግብዓትነት በመውሰድና ክፍተቶችን በማስወገድ በሀገሪቱ ያለውን የዘርፉን አቅም በአግባቡ መጠቀምና ከውጭ የሚገባውን ምርት ማስቀረት እንደሚገባም በውይይቱ ተነስቷል።
የጥጥ መሬት ሽፋን መጨመር፣ ለአልሚዎች የግብይት ሥርዓት እና የገበያ ዋስትና መስጠት ዘርፉ ያሉበትን ችግሮች ለፍታት በመፍትሔነት ተጠቁመዋል፡፡ የንቅናቄ መድረኩ የተሻለ የጥጥ ምርት በሚመረትባቸው አርባምንጭ እና ጋንቤላ የሚቀጥል ይሆናል ተብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- መሠረት ባዬ – ከጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleኢትዮጵያ ጠንካራ የግል መረጃ ጥበቃ ሥርዓት ለመዘርጋት ያስችላል የተባለ “የግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ” ተግባራዊ ልታደርግ ነው።
Next article‹‹አሁንም በመርዛማ ወሬያችሁ ልታንበረክኩን አትችሉም። ይህንም ታሪክ እንደ ዓደዋው ድል ዳግም ዓደዋ ተብሎ እንደሚወሳ እርግጠኞች ነን›› ኮሎኔል ጌትነት አዳነ