
ኢትዮጵያ ጠንካራ የግል መረጃ ጥበቃ ሥርዓት ለመዘርጋት ያስችላል የተባለ “የግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ” ተግባራዊ ልታደርግ ነው።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አዋጁ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን የግል መረጃ ጥበቃ ተመርኩዞ ግልሰቦች በግል መረጃቸው ላይ ያላቸውን ዝርዝር መብትና ጥበቃ የሚደነግግ ነው። እስከ አሁን የሰዎች የግል መረጃ የማቀናበር መርሆዎች ባለመቀመጣቸውና የግል መረጃ ተቆጣጣሪ አካል ባለመሰየሙ በኢትዮጵያ ጠንካራ የግል መረጃ ጥበቃ ሥርዓት ሳይዘረጋ ቆይቷል።
በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ አዋጅ በኢትዮጵያ የግል መረጃ ጥበቃ ሥርዓት ዓለምአቀፋዊ ደረጃዎችን በጠበቀ መልኩ የግል መረጃ ከሀገር ውስጥ ወደ ውጭ ሀገር፣ ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር ውስጥ በማዘዋወር መልካም እድሎችን አሟጦ መጠቀም አስፈላጊ ኾኖ በመገኘቱ ነው የተረቀቀው ተብሏል።
አዋጁ የማንኛውም ግለሰብ መረጃ ሲቀናበር የግላዊ መብቱን ባከበረ መልኩ እንዲሆን የሚደነግግና ጥንቃቄ የሚፈልጉ መረጃዎችን ማቀናበርን የሚከለክል ነው።
ለህክምና ዓላማ ተፈልጎ በሐኪም ቤት ከተከናወነና በፍርድ ሂደት ከተወሰነ ማቀናበርን የሚፈቅደው አዋጁ በኢትዮጵያ ጠንካራ የግለሰብ መረጃ ጥበቃ ሥርዓት ለመዘርጋት ያስችላልም ነው የተባለው፡፡
ለየትኛውም ዓላማ የተቀናበረ የግለሰብ መረጃ አስፈላጊ ከሆነበት ጊዜ በላይ መቀመጥ እንደሌለበት የሚደነግገው አዋጁ መረጃውን የሰበሰበው የተፈቀደለት አካልም መረጃውን ለሦስተኛ ወገን አሳልፎ ለመስጠት በ3ኛ ወገን የስልጣን ክልል ውስጥ ተገቢው ጥበቃ እንደሚደረግ ሲያረጋግጥ ብቻ መሆኑን ይደነግጋል።ጥንቃቄ የሚፈልግ የግል መረጃን ከሀገር ውጪ ለማስተላለፍ በቅድሚያ የኮሚሽኑን ፍቃድ ማግኘት እንደሚኖርበት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
አዋጁ የዲጂታል ከባቢ ሁኔታን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ተዓማኒ የመረጃ ልውውጥ በመፍጠር ግለሰቦች ከደኅንነት ስጋት እንዲላቀቁ ያስችላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ