
“አሜሪካ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የጣለችው የጉዞ እገዳ የኢትዮጵያን እና የአሜሪካን የ120 ዓመታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸው መንግሥት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ በማቅረብ እና አካባቢውን ለረጅ ድርጅቶች ክፍት አድርጎ ሳለ የአሜሪካ ውሳኔ ግን የራሷን የጥቅም ፍላጎት የማሳከት ዓላማን የያዘ ነው ብለዋል።
አሜሪካም ምክንያት አድርጋ ያቀረበችው በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ አልደረሰም የሚለው ሀሰት ነው፤ በአሁኑ ወቅት ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ተደራሽ ሆኖ ሳለ እንዳልተደረገ መጠየቋ ዓላማዋ የሌላ ጥቅም እና ፍላጎት አንጅ ምክንያት እንዳልሆነ ቃል አቀባዩ አብራርተዋል።
በመግለጫው የካናዳ ኢምባሲ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ እና ድርድሮች ውይይት በበይነ መረብ እንደተካሄደም አንስተዋል፡፡
በኒዮዎርክ፣ በኒውጀርሲ እና ኮኔክቲከት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአሜሪካ ሴኔት ያልተገቡ ውሳኔዎችን በመቃወም እና ትክክለኛ ሃሳብ እንዳልሆነ አስረድተዋል።
አሜሪካ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የጣለችው የጉዞ እገዳ የኢትዮጵያን እና የአሜሪካን የ120 ዓመታት ዲፕሎማሲ ግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስገንዝበዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ግንኙነቷን እንደምታጤነው ተናግረዋል። የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከአልሸባብ ዘመቻ በፊት እንኳን በኮሪያ ዘመቻ በብቸኝነት ከአፍሪካ የአሜሪካ አጋር ሆና የነበረችው ኢትዮጵያ በመሆኗ ግንኙነቱ ሲበላሽ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አሜሪካም ተጎጅ እንደምትሆን ተናግረዋል።
አሜሪካ የወሰነችውን ውሳኔ እንድታጤነው እና ያለን ግንኙነት እንዲቋረጥ አንፈልግም ነው ያሉት። በምንም መልኩ ግን ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷ እንዲነካ አትፈቅድም ብለዋል።
ኢትዮጵያ የኬሚካል የጦር መሳሪያ ተጠቅማለች የሚለው ሃሳብ ስህተት እና ረብ የሌለው መሆኑንም ተናግረዋል።
በአውሮፓ የተቋቋመው ለኢትዮጵያ ዘብ እንቁም “እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ” በሚል የበይነ መረብ እና ማኅበራዊ ሚዲያ ውጤታማ ዘመቻ አካሂዷል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡- አንዷለም መናን- ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ