“አንዳንድ ሀገራት በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ በመግባት አዛዥ ናዛዥ ለመሆን እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ተቀባይነት የለውም” በአውስትራሊያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን

106
“አንዳንድ ሀገራት በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ በመግባት አዛዥ ናዛዥ ለመሆን እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ተቀባይነት የለውም” በአውስትራሊያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአውስትራሊያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ የበይነ መረብ ውይይት አካሂደዋል።
በአውስትራሊያ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶክተር ሙክታር ከድር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ ሰጥተዋል፡፡ በገለጻቸውም አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያ ላይ ያደረሰውን ጥፋት ተከትሎ የተወሰደውን ሕግ የማስከበር እርምጃና ሂደቱ ያለበትን ደረጃ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ከግብፅና ከሱዳን መንግሥታት ጋር እየተካሄደ ያለውን ድርድርና የግድቡ ግንባታ አሁን የደረሰበትን ምዕራፍ እንዲሁም 6ኛው ብሔራዊ ምርጫን ለማከናወን እየተደረጉ ያሉትን ዝግጅቶችና የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይን በሚመለከት መረጃ በመስጠት የመንግሥትን አቋም ገልጸዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ የዳያስፖራ አባላት አሸባሪው የሕወሓት ቡድን የፈጸመው ጥፋት በፍጹም ይቅር የማይባል ወንጀል መሆኑንና መንግሥት የወሰደውን ህግ የማስከበር እርምጃ ተከትሎ ከቡድኑ ጋር በቀጥታና በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸው አካላት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር የሚያደርጉትን የተቀናጀ እንቅስቃሴ መከላከል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በአሸባሪውሕወሓት ደጋፊዎች አማካኝነት እየተሰራጩ ያሉ የሐሰት መረጃዎችን አጥብቀው እንደሚያወግዙ ይህንንም ለማክሸፍ በዳያስፖራ አባላት የተጠናከረ እንቅስቃሴ እንዲካሄድ፣ የተወሰደውን እርምጃ ተከትሎ አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት አዛዥ ናዛዥ ለመሆን እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ተቀባይነት እንደሌለው እንዲሁም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳር እንዲደርስ ከዚህ በፊት የጀመሯቸውን የድጋፍ ሥራዎች አጠናክረው እንደሚቀጥሉ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የአሜሪካ የጉዞ ክልከላ የእጅ አዙር ፍላጎትን ለማስፈጸም ያለመ ነው” የፖለቲካ ሳይንስ መምህር
Next article“አሜሪካ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የጣለችው የጉዞ እገዳ የኢትዮጵያን እና የአሜሪካን የ120 ዓመታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር