“የአሜሪካ የጉዞ ክልከላ የእጅ አዙር ፍላጎትን ለማስፈጸም ያለመ ነው” የፖለቲካ ሳይንስ መምህር

112
“የአሜሪካ የጉዞ ክልከላ የእጅ አዙር ፍላጎትን ለማስፈጸም ያለመ ነው” የፖለቲካ ሳይንስ መምህር
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ከመሠረተችው የውጭ ግንኙነት መካከል የአሜሪካ ዘመናት ያሳለፈው ወዳጅነት ይጠቀሳል፡፡ ከ1900ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ሁለቱ ሀገራት ጥብቅ ትስስር መስርተው በስኬት ዘልቀዋል፡፡ በባለብዙ ግንኙነት ማዕቀፍ ውስጥ በመካተትም ዓለም አቀፍ ችግሮችን በጋራ ተጋፍጠው ውጤትም አስመዝግበዋል፡፡ ኢትዮጵያ በተለያዩ ሀገራት ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት ተሰሚነቷን ከፍ አድርጋለች፡፡
ሶማሊያን በማረጋጋት፣ ዘመናት ያስቆጠረውን የደቡብ ሱዳን ፖለቲካዊ ውጥንቅጥን እልባት በመስጠት፣ የሱዳንን የፖለቲካ ሳንካ መስመር በማስያዝ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆናለች፡፡ በሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ በላይቤሪያ እና ሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት የተረጋጋ መንግሥት እንዲኖር ጥረት አድርጋ ውጤት አስገኝታለች፡፡
አሜሪካ ሽብርተኝነትን ከመዋጋት ጀምሮ በቀጣናው በምታደርገው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ አጋር በመሆን ሠርታለች፡፡ ነጻ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የምታራምደው ኢትዮጵያ የሀገራትን ጥቅም ሳትነካ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ጥብቅ የወዳጅነት ግንኙነት መሥርታለች፡፡ ከአሜሪካ ጋር ያላት መልካም ግንኙነት የዚህ ነጸብራቅ ማሳያ መሆኑን በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ጀማል ሰዒድ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም የአሜሪካ መንግሥት የሁለቱን ሀገራት የግንኙነት ታሪካዊ ዳራ የማይመጥን፣ በመካከላቸው የነበረውን መልካም፣ ውጤታማ እና ዘመን አይሽሬ ግንኙነት የሚያሻክር ውሳኔ አሳልፏል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ጅምላ ጭፍጨፋ ሲፈጽም አይታ እንዳላየች፣ ሰምታ እንዳልሰማች ያለፈችው አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ውሳኔ እንድታሳልፍ የሚያደርግ ምክንያት እንደሌለ አቶ ጀማል አብራርተዋል፡፡ ለውሳኔው መነሻ ይሆናሉ ያሏቻውን ነጥቦችም ዘርዝረዋል፡፡ የትራምፕን የውጭ ጣልቃ ገብነት ፖሊሲ ማስቀጠሏና አሜሪካ የምታራምደው ጂኦፖለቲካዊ የለውጥ አቋም የተበላሸ መሆኑ ለውሳኔው መነሻ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጉዳዮች፣ በምርጫና በመልካም አስተዳደር እና በሌሎች ጉዳዮች ጣልቃ መግቢያ በሮች በኢትዮጵያ መዘጋቱ የአሜሪካን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ የሚጻረር በመሆኑ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን አቋም እንድትቀይር ይገፋፋታል፡፡ በተለይ ከቻይና ጋር ያላትን ተቃርኖ በአፍሪካ ውስጥ ለማስፈጸም የሄደችበት መንገድ አፍሪካን ለአደጋ የሚዳርግና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚነካ እንደሚሆን የፖለቲካ መምህሩ ገልጸዋል፡፡
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር የአሜሪካ ሚና ማነሱ ሌላኛው ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት በኩል እልባት እንዲያገኝ ፍላጎት ማሳደሯ፣ የአፍሪካ ሀገራት የሚያሳዩት ጠንካራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ እንቅፋት እንደሚሆን በመስጋት ነው፡፡
በአፍሪካ የቻይና፣ የሩሲያና የቱርክ ሚና ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ትብብር እያደገ መሄድ ለአሜሪካ አልተዋጠላትም ይላሉ የፖለቲካ መምህሩ፡፡ አሜሪካን ጨምሮ የአውሮፓ ሀገራት አፍሪካ በድህነት እንድትታሰር ይፈልጋሉ፡፡ በተለይ የአሜሪካ ኩባንያዎች የአፍሪካን ማዕድናት ለማጋዝና የተፈጥሮ ሃብቷን ለማጋበስ ካላቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ እድገቷን አይፈልጉትም፡፡ ለዚህም ሀገራቱና የአፍሪካ ሕብረት ሥሪት የአሜሪካን ጥቅም በሚያስከብር መልኩ እንዲሆን ይሻሉ፡፡ ለዚህም በአፍሪካ ቀንድ ጠንካራ አቋም ያላትን ሀገር ጫና ማሳደር እንደ አማራጭ ሊወስዱ ይችላሉ፡፡
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወዳጅነት አዲስ ክፍለ አህጉራዊ ኀይል ሊፈጥር ይችላል በሚል በአሜሪካ ላይ ስጋት ደቅኗል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ጥምረት የኀይል አሰላለፉን በመቀየር፣ የግብጽን የበላይነት ያዳክማል፣ ይህም አሜሪካ በግብጽ በኩል ከመካከለኛው ምሥራቅ የምታገኘውን ጥቅም ያሳጣታል፡፡ በዚህም መነሻነት ኢትዮጵያ ላይ ያላትን አቋም እንድትቀይር ሳያደርጋት እንዳልቀረ አብራርተዋል፡፡ ይህም በቀጣናው ብቻም ሳይሆን በመላ አፍሪካ ጉልህ ተጽዕኖ እንዳይፈጥር ተሰግቷል፡፡
ኢትዮጵያ የተከተለችው አካሄድ ሉዓላዊነቷን የሚያስጠብቅ፣ በውስጧ ጉዳይ ጣልቃ ገብነትን የሚከለክል፣ ነፃ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋን ተጠቅማ ከፈለገችው ሀገር ጋር ግንኙነት ለመመስረት በሚያስችል ሀቅ ላይ ተመስርታ ነው፡፡ ይህም በአሜሪካ ጥቅም ላይ ምንም ተጽዕኖ የሚያሳድር አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ በአሜሪካ በኩል ጣልቃገብነትን በኀይል የማሳካት ፍላጎት እንዳለ ጠቅሰዋል፡፡
ምንም እንኳን ክልከላው የጎላ ተጽዕኖ ባይኖረውም ኢትዮጵያ ውሳኔው ትክክል አለመሆኑንና አሜሪካ አቋሟን እንድትቀይር በአውሮፓ ሕብረት ላይ ግፊት ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ኀያላን ሀገራት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ፉክክር ውስጥ በመግባት ተጽዕኖ እንዳያሳርፉ በሁሉም ወገን ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቅ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ መከተል ይኖርባታል ነው ያሉት፡፡
“የውስጥ አንድነታችን ወደ ውጪ ለምናደርገው እንቅስቃሴ መነሻ ነው” ያሉት መምህሩ የኢትዮጵያ የውስጥ ሁኔታ ለምትከተለው የውጭ ግንኙነት አቋም አጋዥ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ ለዚህም በውስጥ ዲፕሎማሲ ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከርና የመንግሥት ቅቡልነትን ማሳደግ እና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ መክረዋል፡፡
አሜሪካ የጣለችው ቪዛ ክልከላ ነፃ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸውን ለመከተል የጀመሩ ሀገራትን ለማደናቀፍ በሌሎች ሀገራት ላይ ጭምር እንደተጣለ ታስቦ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት በጋራ መታገል ይገባቸዋል፤ የአፍሪካ ሕብረት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲያደርግና የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ በአዲስ እንዲጎመራ ግፊት ማድረግም ከኢትዮጵያ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በመርህ ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ እንደሚጠይቅም መምህር ጀማል አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የወልቃይት እውነት ቅድመ ሕወሃት”
Next article“አንዳንድ ሀገራት በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ በመግባት አዛዥ ናዛዥ ለመሆን እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ተቀባይነት የለውም” በአውስትራሊያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን