
“ኢትዮጵያ ለመገናኛ ብዙኀን ነፃነት እና ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት መረጋገጥ ቁርጠኛ ናት” የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለስልጣን
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 16/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የመገናኛ ብዙኀን ነፃነት እና ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠ ነው። መንግሥትም ለነዚህ መብቶች መከበር ቁርጠኛ አቋም አለው። ይህንንም በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል ያለው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለስልጣን ባለፉት ሦስት ዓመታት የሀሳብ ብዝሃነት ምህዳር እንዲሰፋ ተከታታይ ለውጦች መደረጋቸውን ገልጿል።በዚህም ጋዜጠኞችና የፓለቲካ እስረኞች እንዲለቀቁ ማድረጉ መንግስት ከወሰዳቸው እርምጃዎች ውስጥ እንደሚጠቀስ ገልጿል።
የሀገር ውስጥና የባህር ማዶ ጋዜጠኞች መረጃ ያለምንም ችግር እንዲያገኙ ለማድረግ ከለውጡ በፊት የነበሩ ክልከላዎችን በማስቀረት ማሻሻያ አድርጓል ነው ያለው ባለስልጣኑ።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ቋሚ መቀመጫቸውን ካደረጉ 129 ጋዜጠኞች ከ35 የውጭ ሀገር የመገናኛ ብዙኀን ተቋማት ፍቃድ ተሰጥቷቸው እየሠሩ እንደሚገኙ አስታውቋል። በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅትም ቢሆን ከተለያዩ ሀገራት የተወጣጡ 82 የውጭ ሀገር ጋዜጠኞች በትግራይ ክልል የዘገባ ሽፋን እንዲሰጡ እንደተፈቀደላቸው አመላክቷል።
ይሁን እንጂ የሕግ ጥሰት ሲያጋጥም በየትኛውም የዓለም ክፍል እንደሚደረገው ሁሉ ባለስልጣኑ ሕግን የማስከበር ኀላፊነቱን የመወጣት ግዴታ እንዳለበት አስታውቋል።
በመሆኑም መንግሥት ሃሳብን በነጻነት መግለጽንና የፕሬስ ነጻነትን በተመለከተ የያዘው አቋም የማይናወጥ መሆኑን ገልጾ ሀገሪቷም ሆነች ባለስልጣኑ በቅንነት ሥራቸውን የሚሠሩ ጋዜጠኞችን ለማስተናገድ ዝግጁ ናቸው ብሏል። መረጃው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለስልጣን ነው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m