በአማራ ክልል አርሶ አደሩን መሠረት ያደረገ የገንዘብ ቁጠባ ፌደሬሽን ሊመሠረት ነው፡፡

226

በአማራ ክልል አርሶ አደሩን መሠረት ያደረገ የገንዘብ ቁጠባ ፌደሬሽን ሊመሠረት ነው፡፡

ፌደሬሽኑ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትና ዩኒየኖች የሚገጥማቸውን የገንዘብ እጥረት ይቀርፋል ተብሏል፡፡

ባሕር ዳር፡ መስከረም 7/2012 ዓ.ም (አብመድ) ለኑሮው በየዕለቱ መናር ከሚጠቀሱ ዋና ዋና ችግሮች መካከል የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትና ዩኒየኖች በሀገር ውስጥ ገበያ ጠንካራ ተዋዳዳሪ አለመሆን ነው፡፡ በነባራዊ ገበያው ተወዳዳሪ ሊያደርግ የሚችል የካፒታል እጥረት መኖር ደግሞ የችግሩ መንስኤ እንደሆነ ነው የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ያነጋገራቸው ማኅበራትና ዩኒየኖች የጠቆሙት፡፡ ለግብርና መሠረታዊ አቅርቦቶች ብድር የሚሰጥ አበዳሪ የገንዘብ ተቋም አለመኖሩ ደግሞ ጉዳዩን የከፋ አድርጎታል፡፡

የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ በክልሉ የሚገኙ ኅብረት ሥራ ማኅበራትና ዩኒየኖች እየገጠማቸው ያለውን የገንዘብ ችግር ለመፍታት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ኅብረት ሥራ ማኅበራት የግብርና ምርቶችን ከአርሶ አደሩ ተረክበው ለገበያ ማቅረብ የሚያስችላቸውን አቅም ለመፍጠርም የገንዘብ ቁጠባ ፌደሬሽን ለመመሥረት በሂደት ላይ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኃይለልዑል ተስፋሁን ለአብመድ እንደተናገሩት የገንዘብ ቁጠባ ፌዴሬሽኑን ለመመሥረት አባላቱን በፌደሬሽኑ አስፈላጊነት ዙሪያ እያወያዬ ነው፡፡ በክልሉ ካሉት 70 ዩኒየኖች መካከል 43 በአመሠራረቱ ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸውም ተጠቁሟል፡፡ ፌደሬሽኑ አስፈላጊውን ሕጋዊ ዕውቅና እንዳገኘና የአደረጃጀት መመሪያውን እንዳዘጋጀም ነው የተነገረው፡፡

የገንዘብ ቁጠባ ፌዴሬሽኑ የግብርና ምርት አቅራቢውም ይሁን ሸማቹ የቁጠባና የብድር አገልግሎት የሚያገኝበት ይሆናልም ተብሏል፡፡ የቁጠባ ፌዴሬሽኑ ዕውን እስኪሆን ድረስ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ከልማት ባንክ 972 ሚሊዮን ብር ብድር ለማግኘት በሂደት ላይ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ሀይሉ ማሞ

Previous articleምሽት12:00 ዜና ሙዳይ ባሕር ዳር፡ መስከረም 07/2012 ዓ.ም (አብመድ)
Next articleየሀሰት ሪፖርትን ለመከላከል ማዕከላዊ የመረጃ ቋት እያቋቋመ መሆኑን የግብርና ትራስፎርሜሽን ኤጄንሲ አስታወቀ፡፡